7ኛው የአውሮፓ ህብረትና የአፍሪካ መሪዎች የጋራ ጉባኤ በሉዋንዳ - አንጎላ
Description
7ኛው የአውሮፓ ህብረትና የአፍሪካ መሪዎች የጋራ ጉባኤ በሉዋንዳ - አንጎላ
7ኛው የአውሮፓና አፍሪካ የመሪዎች ጉባኤ ለሁለት ቀናት በአንጎላ ዋና ከተማ ሉዋንዳ ሲካሄድ ቆይቶ፤ ዛሬ ማምሻውን ልዩ ልዩ ውሳኔዎችን በማሳለፍና የጋራ መግለጫ በማውጣት ተጠናቋል። 55 የአፍሪካና 27 የአውሮፓ አገሮች የተሳተፉበትና 49 የአገር መሪዎች የተገኙበት ይህ ጉባኤ፤ የተከሂደው የሁለቱ አህጉሮች የጋራ ወዳጅነት 25ኛ ዓመቱን በያዘበት ወቅት፤ ግን ደግሞ ዓለምአቀፍ የንግድ ስርዓቱ እና ግንኙነቱ በውጥረት ውስጥ በሆኑበት ግዜ በመሆኑ ልዩ ትኩረት ተስቶታል።
ጉባኤው በአስተናጋጇ አገር አንጎላና በአውሮፓ ህብረትፕሬዝዳንቶች ሚስተር ጃኦ ሎሬንሶና ሚስተር አንቶኒዮ ኮስታ ነበር በጋራ የተመራው። በጉባኤው መክፈቻ የአውሮፓ ኮሚሽን ፕሬዝድነት ወይዘሮ ኡርሱላ ቮንዴርሌየን፤ ወቅቱ አውሮፓ ህብረትና አፍሪካ ከመቼውም ግዜ ይበልጥ የሚቀራረቡበትና በጋራ የሚሰሩበት ግዜ መሆኑን አስገንዝበዋል። “ በአሁኑ ዓለምአቀፉ የኢኮኖሚ ፍጥጫ ባአየለበት ወቅት አፍርካ እና አውሮፓ ከመቼውም ግዜ ይበልጥ መቀራረብና በጋራ መስራት ይኖርባቸዋል” በማለት ዛሬ ወደ ሉዋንዳ ያመጣቸውም ይኸው መሆኑን አስታውቀዋል።
ወይዘሮ ቮንዴርላየን ካለፈው ጉባኤያቸው ወዲህ ከተሰራውና ከተገኘው በላይ እንደ ነባር ወዳጆች፣ የንግድና ኢንቨስትሜንት አጋሮች አውሮፓና አፍሪካ ተፈቃቅደው የተገናኙ አጋሮች መሆናቸውን ማረጋገጥ አለብን ብለዋልም።
የእፍሪካ ኮሚሽን ፕሬዝዳንት ማሳሰቢያ
የአፍሪካ ኮሚሺን ፕሬዚዳንት ሚስተር ማህሙድ አሊ የሱፍ በበኩላቸው አውሮፓ ከዚህ ቀደም በበቂ ሁኔታ በአፍሪካ ኢንቨስት አድርጓል ማለት እንደማይቻል አስታውሰው፤ እንደ ወዳጅነታቸዋና አጋርነታቸው ብቻ ሳይሆን፤ አፍሪካ የወደፊቱ ተስፋ መሆኑን በመረዳት ብዙ የሚጠበቅበት መሆኑን አስገንዘበዋል። “አፍሪካ መጭው የዓለም እድገት ምንጭ መሆኗ የማያጠራጥር በመሆኑ በጋራ ኢንቨስት ማድረግ ይኖርብናል። የአውሮፓ ኩባንያዎች በአፍሪካ መዋዕለ ንዋይቸውን ቢያፈሱ ተጠቃሚዎቹ እነሱም ናቸው” በማለት የዓለም የወደፊት ተስፋ አፍሪካ ውስጥ ነው ብለዋል።
መሪዎቹ የተስማሙባቸውና ውሳኔ ያስለፉቫቸው አጀንዳዎች
መሪዎቹ በዓለምአቀፍ ደረጃ የባለብዙ ወገን ግንኙነቶችን በማጠናከር የመንግስታቱ ድርጅትን የማሻሻያ አጀንድዎች ተግባራዊ ለማድረግ፤ የቡድን 20 ከመሳሰሉ ዓለምአቀፍ ስብስቦች ጋር በጋራ ለመስራት፤ የዓለም የገንዘብ ተቋማትን አሰራር እንዲሻሻል የጋራ ጥረት ለማድረግና የአየር ንብረት ለውጥ አጀንዳዎችን ለማስፈጸም በጋራ ለመስራት የተስማሙ መሆኑ ተገልጿል።
ጉባኤው የሁለቱን ወገኖች የንግድ መጠን ለማሳደግና ለማሳለጥ የሚያስችሉ ስልቶችንና አሰራሮችን ለመዘርጋት የተስማማ መሆኑም ታውቋል። ፈላስያንና ስደተኞችን በሚመለከትም መሪዎቹ ሁለቱንም ወገኖች ተጠቃሚ የሚያደርጉ መግቢያና መውጫ መንገዶችን ለመፈለግና የደንበር ቁጥጥሮችንም ለማጠናከርና የሰው አዘዋዋሪ ወንጀለኖችን ለመቆጣጠር ተማምተዋል ተብሏል።
ታዛቢዎች በአፍርካና የአውሮፓ ህብረት ወዳጅነትና አጋርነት
ይሁን እንጂ ባለሙያዎች እንደሚሉት የአፍርካና አውሮፓ ግንኙነት እና አጋርነት በተፈለገው መጠን እያደገና ውጤትም እያስገኘ አይደለም። በየወቅቱ በሚካሄዱ ጉባኤዎች መግለጫዎችን ከማውጣት ባለፈ ብዙም ተጨባጭ ውጤቶች የታዩባቸው አይደሉም። በአሁኑ ወቅትም ብዙዎቹ የእፍሪካ አገሮች እንደ ቢሪክስና ቡድን 20 ወደ መሳሰሉ ስብስቦች እያማተሩ በመሆናቸው የአውሮፓ ዋና የአፍርካ ወዳጅና አጋር ሆኖ መቀጠል እየቀንሰ ነው፤ እንደ ባለባለሙያዎቹ አስተያየት።
ከዚህም በተጨማሪም የአውሮፓና አፍርካ ግንኙነት አሁንም የተረጅና እረጂ አይነት የኮሊኒያል አስተሳሰብ ያጠላበት እንደሆነም ይነገራል። በቻትህም ሀውስ የአፍሪካ ዳይሬክተር የሆኑት ወይዘሬት ትግስቲ አማረ ግንኙነቱ አሁንም ከዚህ አይነቱ የቆየ ግንኑነት የተላቀቀ ነው ማለት እንደማይቻል ነው የተናጋሩት። “ ግንኑነቱን የእኩሎች ግንኙነት ብሎ ምደምደም ያስችግራል። የዚህ አይነቱ የሰጭና ተቀባይ ግንኙነት የአፍርካንና አውሮፓን ግንኙነት ለብዙ ዓመታት ውስብስብ አድርጎት ነው የቆየው በማለት ሆኖም ግን የአውሮፓ ህብረት ለአፍርካ አሁንም ትልቁ የንግድ አጋር መሆኑን ገልጸዋል።
የሉዋንዳው የአፍሪካና የአውሮፓ መሪዎች የሁለት ቀናት ጉባኤ ፕሬዝዳንት ትራምፕ የሩሲያና ዩክሬንን ጦርነት ለማስቆም ያቀረቡት የሰላም እቅድና የፈጠረው ውዝግብ ተገቢውን ትኩረት እንዳይገኝ እንዳደረገውም እይተዘገበ ነው። 27ቱ የህብረቱ አባል አገራት መሪዎች ከጉባኤው ጎን የራሳቸውን ስብሰባ በማካሄድ በሰላም እቅዱ ላይ በመምከር ውሳኔዎችን ያሳለፉ ሲሆን፤ የዓለም አቀፍ የዜና አውታሮችም ከአፍሪካና የአውሮፓ የመሪዎች ስብሰባ ይልቅ በአዉሮጳ ህብረት ዩክይን ጉዳይ ላይ አተኩረው ተስተውለዋል።
ገበያው ንጉሴ
ታምራት ዲንሳ
ነጋሽ መሐመድ























