ከ18 ዓመት በታች ስደተኞች የሊቢያና የባሕር ላይ መከራ
Description
«የተሻለ መንገድ ቢኖር ኖሮ ማንም ሰው በባሕር ላይ ሕይወቱን ለአደጋ አያጋልጥም ነበር ። ሆኖም ሌላ መፍትኄ የለም ። ለዚያም ነው ሕይወታችንን ለአደጋ የምናጋልጠው ።» የ15 ዓመት አዳጊ ስደተኛ አስተያየት ነው ። የ15 ዓመቱ ጊኒያዊ አዳጊ ይህን የተናገረው በባሕር ላይ ነፍስ አድን ድርጅት ኤስኦኤስ ሂዩማኒቲ ርዳታ በባሕር ከመስጠም በተረፈበት ወቅት ነው ።
ላለፉት ዐሥርተ ዓመታት በባሕር ላይ ነፍስ አድን ተግባር የተሰማራው እና መቀመጫውን በበርሊን ያደረገው መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት ማስጠንቀቂያ አለው ። ከሊቢያ ወይም ቱኒዝያ ሙሉ በሙሉ በተጨናነቁ እና አብዛኛውን ጊዜ ለባሕር ላይ ጉዞ በማይገቡ ጀልባዎች ያለወላጅ ወይንም ሌላ አዋቂ የሚሳፈሩ ሕጻናት እና አዳጊ ወጣቶች ቁጥር በየጊዜው እየጨመረ ነው ። በነፍስ አድን ድርጅቶች ርዳታ በባሕር ከመስጠም ከተረፉት መካከል አንድ አምስተኛው የሚሆኑት ከ18 ዓመት በታች ናቸው ።
የአዳጊ ስደተኞቹ ልጆች ሁኔታ ሊቢያ ውስጥ እጅግ የከፋ ነው
የአባት ስሟ እንዳይጠቀስ የፈለገችው የሥነ ልቦና ባለሞያዋ ኤስተር ባለፈው ሕዳር እና ታኅሣስ ወር «ሂውማኒቲ 1» በተባለው የነፍስ አድን መርከብ ላይ የሥነ ልቦና አገልግሎት ሰጥታለች ። በዚህ ዓመት ብቻ 347 ስደተኞች የታጨቁባቸው ስድስት ጀልቦችን ከመስጠም መታደጋቸውን ተናግራለች ። ከስደተኞቹ መካከል 43ቱ ዕድሜያቸው ከ18 ዓመት በታች አዳጊዎች መሆናቸውንም ጠቅሳለች ። በአካልም በሥነ ልቦናም ብርቱ ጉዳት የደረሰባቸው እነዚህ ልጆች እጅግ ከመዳከማቸው የተነሳም ያላ ወላጅ እና አዋቂ ባሕሩን በማቋረጣቸው ውስጣቸው የዛለ እና ተስፋ የቆረጡ ናቸው ።
«ልጆቹ ለበርካታ ቀናት እና ሌሊት አብዛኛውን ጊዜ ያለ ምግብ እና ውኃ በባሕር ውስጥ ነበሩ፤ በውኃ ጥም የተሰቃዩ፤ በባሕር ላይ ኅመም የተጎዱ ብሎም ከጨው ውኃ እና ነዳጅ ጋር አካላቸው በመገናኘቱም በአብዛኛው ሰውነታቸው የተለበለቡ ነበሩ ። በሚያሳዝን ሁኔታ ብዙዎች ልጆች በሊቢያ ማጎሪያዎች ውስጥ ረዘም ላለ ጊዜ በመቆየታቸው እከክ ወይም ሌሎች የቆዳ በሽታዎች እና ቁስሎች አሉባቸው ። እናም ሁሉም እጅግ ቅስማቸው የተሰበሩ ናቸው ።»
ከማጎሪያዎች ውስጥ ማምለጥ የተሳካላቸው ሌላ የባሕር ላይ ጉዞ ከፍተኛ አደጋ ይጠብቃቸዋል
ከምንም በላይ ደግሞ የእነዚህ ልጆች ሁኔታ ሊቢያ ውስጥ እጅግ የከፋ ነው ። የባሕር ላይ ጉዟቸው ተጨናግፎ በሊቢያn የባሕር ጠረፍ ጠባቂዎች እጆች ላይ የሚወድቁ ልጆች መከራ ደግሞ በቃላት የማይገለጥ ነው ። ሊቢያ ሕገ ወጥ ስደተኞች ወደ አውሮጳ እንዳይመጡ እንድትከላከል በሚል በሚሊዮን ዩሮ የሚቆጠር ወጪ የተካተተበትን ውል ፈርማለች ። እናም አገሪቱ በምትፈጽመው ከፍተኛ የሰብአዊ መብቶች ጥሰት ብርቱ ትችት ይሰነዘርባታል ። ልጆቹ ላይ ሊቢያ ውስጥ ከሚደርስባቸው እንግልት እና መከራ ባሻገር የአስገድዶ መድፈር ወንጀሎችም ይፈጸምባቸዋል ።
«ወጣቶቹ ስለደረሰባቸው ከባድ የፆታ ጥቃት፣ ስቅየት፣ የሕጻናት ጉልበት ብዝበዛ፣ የሚወዷቸውን በሞት ስለማጣታቸው አልፎ ተርፎም በሴቶች ጭምር ስለሚፈጸሙ የሕገወጥ ሰዎች ዝውውር ጉዳዮች ነግረውኛል ። አንዳንዶቹ ወጣቶች በስቅየት ወቅት የደረሰባቸውን ምልክቶቻቸውን ዐሳይተውኛል ። ጠባሳ ነበራቸው፤ ያም ብቻ አይደለም በሊቢያ ማጎሪያዎች ውስጥ እግር እና እጆቻቸው ተጠፍረው ሲሰቃዩ የሚያሳዩ ፎቶግራፎች እና ቪዲዮዎችን ጭምር ዐሳይተውኛል ።»
ከነዚህ ማጎሪያዎች ውስጥ ማምለጥ የተሳካላቸው የሚጠብቃቸው ሌላ የባሕር ላይ ጉዞ ከፍተኛ አደጋ ነው ። የተባበሩት መንግሥታት የሕፃናት መርጃ ድርጅት (UNICEF) የካቲት ወር ላይ ያወጣው መረጃ እንደሚጠቁመው ከሆነ ባለፉት ዐሥር ዓመታት 3500 ሕጻናት በባሕር ላይ ጉዞ ሙከራቸው ሞተዋል አለያም ያሉበት ሳይታወቅ ጠፍተዋል ። ሕጻናቱ ጉዟቸው በሜዲትራኒያን ባሕር ወደ አውሮጳዊቷ ጣሊያን ነበር ። ያ ማለት በየቀኑ አንድ ሕጻን ይሞታል ወይንም ይሰዋወራል ። ያም በመሆኑ እንደ ኤስ ኦ ኤስ ሰብአዊነት ያሉ በባሕር ላይ የነፍስ አድን ተግባራ የተሠማሩ ድርጅቶች የአውሮጳ ኅብረት ከሊቢያ እና ከቱኒዝያ ጋር የጀመረውን የጋር ትብብር በአስቸኳይ እንዲያቋርጥ ጥሪ አስተላልፈዋል። የኤስኦኤስ ሰብአዊነት ዋና ኃላፊ ቲል ሩመንሆህል ከጊዜ ወደ ጊዜ የአዳጊ ተሰዳጆች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን ተናግረዋል ።
«ከተሰዳጆች መካከል ዕድሜያቸው ከ18 ዓመት በታች የሆኑ ልጆች ቁጥር ባለፉት ዐሥር ዓመታት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መጥቷል ። ወደ ጣሊያን ከገቡት ሰዎች መካከል አንድ አምስተኛው ያህሉ አዳጊ ልጆች ናቸው ። በእኛ ነፍስ አድን ተግባር ደግሞ በአማካይ ከአንድ ሦስተኛ በላይ ነው ። በቅርቡ 120 ታዳጊ ሕጻናትን የያዘ ጀልባ አግኝተናል ። ብቻቸዉን ሲጓዙ የነበሩ እነዚህ አዳጊ ልጆች በፍርኃት ተውጠው ከሊቢያ የባሕር ጠባቂዎች ፊት እየዘለሉ ወደ ባሕር ገቡ ።»
የአሜሪካ ዓለማቀፍ ተራድዖ ድርጅት ርዳታ መቋረጥ ብርቱ ተጽእኖ ፈጥሯል
ዩናይትድ ስቴትስ በአሜሪካ ዓለማቀፍ ተራድዖ ድርጅት (USAID) በኩል ትሰጥ የነበረውን ርዳታ ማቋረጧ በስደተኞች ቁጥር መጨመር ላይ የራሱ አስተዋጽኦ አለው ። «ዘ ላንሴት» የተሰኘው መጽሔት እንደዘገበው ከሆነ፦ የዩኤስኤአይዲ ርዳታ ቅነሳ በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት ውስጥ አምስት ሚሊዮን ሕፃናትን ጨምሮ ከ14 ሚሊዮን በላይ ሰዎችን ለሞት ሊዳርግ ይችላል ። ጀርመንም ወደ አንድ ቢሊዮን ዩሮ የሚጠጋ የልማት ርዳታዋን አቋርጣለች ። በትናንሽ መናኛ ጀልባዎች የሚሳፈሩ ሕጻናት እና አዳጊ ወጣቶች ቁጥር ወደፊት ሊጨምር እንደሚችል የዓለም አቀፉ ኤስኦኤስ የሕፃናት መንደር ምክትል ኃላፊ አስጠንቅቀዋል ።
«ይህ ብዙ ልጆች በዚህ መስመር እንዲሄዱ የሚያደርግ የማንወጣው አዙሪት ውስጥ ያስገባናል ። ሶማሊያን ብንወስድ አገሪቱ 80 በመቶው በዩኤስኤይድ ጥገኛ ነበረች ። ባለፉት ዓመታት በሶማሊያ አራት ሚሊዮን ተኩል ሕፃናትና ወጣቶች ደርሰናል፣ በዚህ ዓመት ብቻ ቁጥሩ ወደ 1.3 ሚሊዮን ደርሷል ። ያ ለምን ሆነ? ምክንያቱም፦ እነዚህ ሕጻናት እና ወጣቶችን ለመንከባከብ የታቀዱት መጠሊያ ጣቢያዎች ከበጋው ወራት ጀምሮ ባዶ ናቸው ።»
በባሕር ላይ ነፍስ አድን ተግባር የተሰማራው ኤስኦኤስ ሂውማኒቲ የተሰኘው ድርጅት በ2026 ሌላ የነፍስ አድን መርከብ በሜዲትራንያን ባሕር ላይ እንደሚያሰማራ ዐሳውቋል ። ይህም በዋናነት የስደተኞች ጀልባዎችን ፍለጋ እና በቱኒዚያ የባህር ጠረፍ ላይ የሚደርሰውን የሰብአዊ መብት ጥሰት ለመቆጣጠር ነው ተብሏል ። የጀርመን ፌደራል መንግስት በበኩሉ በባሕር ላይ ነፍስ አድን ተግባር ለተሰማራው መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት እንቅስቃሴ ይሰጥ የነበረውን ዓመታዊ የሁለት ሚሊዮን ዩሮ የገንዘብ ድጋፍ አቋርጧል ። ይህ ራሱን የቻለ ሌላ ብርቱ ተግዳሮትን ደቅኗል ።
ማንተጋፍቶት ስለሺ/ኦሊቨር ፒፐር
አዜብ ታደሰ























