የቦሮ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ገዢውን የብልጽግና ፓርቲ ለመዋሃድ ወሰነ
Description
የቦሮ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ገዢውን የብልጽግና ፓርቲ ለመዋሃድ መወሰኑ
በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የሚንቀሳቀሰው ተቃዋሚው የቦሮ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ቦዴፓ ከገዢው የብልጽግና ፓርቲ ጋር መዋሃድ የሚያስችለውን ውሳኔ አሳለፈ። ቦዴፓ ትናንት ሰኞ መተከል ቡለን ውስጥ ባካሄደው 2ኛ አስቸኳይ ድርጅታዊ ጉባኤ ከገዚው ፓርቲ ጋር ለመዋሃድ በአብላጫ ድምጽ መወሰኑን የፓርቲው ሊቀመንበር አቶ አመንቲ ጊሼ ለዶቼ ቬለ ተናግረዋል። ፓርቲውን ወክለው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል የሆኑት ዶ/ር መብራቱ አለሙ ውህደቱ የግለሰቦችን ጥቅም ለማስጠበቅ የተፈጸመ በማለት በይፋ ተቃውመዋል።
የቦሮ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ በቤኒሻንጉል ጉምዝ የክልላዊ ፓርቲ ዕውቅና አግኝቶ የተመሰረተው ከአምስት ዓመት በፊት በ2013 ዓ/ም ነበር። ፓርቲው ከምስረታው ማግስት ጀምሮ ከተቃዋሚነት ይልቅ ከገዚው ፓርቲ ጋር ተቀራርቦ ይሰራ እንደነበር የፓርቲው ባለስልጣናት ጭምር በይፋ ሲገልጹ ቆይተዋል። ትናንት ሰኞ ከወደ መተከል የተሰማው ዜና ግን በቦሮ ሺናሻ ህዝብ ስም የተመሰረተው ፓርቲ ህልውናው ከስሞ ከገዢው ፓርቲ ጋር ውህደት መምረጡን የሚያመላክት ነበር ። የፓርቲው ሊቀመንበር ስለውህደቱ ለዶቼ ቬለ እንዳሉት ፓርቲው የማህበረሰቡን ጥቅም ለማስጠበቅ ሲል ውህደትን መርጧል።
« አጠቃላይ ድርጅቱ ያለበትን ኹኔታ ገምግሞ የማህበረሰቡን አጠቃላይ የሚታገልለትን አጀንዳም በጥልቀት ገምግሞ ውይይት ነበር ያካሄደው ፤ ከጉባኤው በፊት ቅድመ ጉባኤ ኮንፈረንሶች ስናካሂድ ነበር ለሁለት ቀን። በኋላ ጉባኤውን አካሂደን አንድ ቁልፍ ዉሳኔ አስተላልፈናል። ከብልጽግና ፓርቲ ጋር በውህደት የመስራት ዉሳኔ»
ውህደቱን ማን አነሳሳው ? ገዢው ወይስ ፓርቲው ?
ሊቀመንበሩ እንደሚሉት እርሳቸውን ጨምሮ አንዳንድ የፓርቲው አመራሮችበክልሉ መንግስት የተለያዩ መዋቅሮች ውስጥ የአመራር አባል መሆናቸውን ጨምሮ «መልካም ውጤት አስገኝቷል» ያሏቸው ግንኙነቶች ከገዢው ፓርቲ ጋር ለመዋሃድ እንዳነሳሳቸው ነው የተናገሩት ።
«ሃሳቡን በርግጥ ከመንግስት ጋር በጋር ለመስራት ስምምነት ከዚህ በፊት እኔው ራሴ የተቋም ካቢኔ ኾኜ ነው የምሰራው ለአምስት አመት ፤ ሌሎችም በወረዳ ላይ ፣ በዞን ላይ እንደዚህ ተመድበን ነው የምንሰራው እና ይኼ አብሮ መስራት መልካም ውጤት አምጥቶ በአጠቃላይ ፖሊሲዎቻችን እና ስትራቴጂዎቻችን እንዲሁ በጋራ ስንገመግም እና ስንወያይ ነው የቆየነው እና በሂደት ሃሳቡ በእኛ በኩል የተነሳው ግን በነሱ በኩልም ተቀባይነት ነበረው።»
ቦዴፓ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰኔ 16 ቀን 2016 ዓ/ም የ6ኛው ዙር ቀሪና የድጋሚ ምርጫ ካካሄደባቸው ክልሎች አንዱ በነበረው የቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል አንድ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫን ጨምሮ በክልል እና በተዋረድ ባሉ ምክር ቤቶች መግባት የሚያስችለውን ድምጽ ማግኘቱ ይታወሳል።
የህዝብ ተወካዩ ተቃውሞ
ፓርቲውን ወክለው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል የሆኑት ዶ/ር መብራቱ ዓለሙ የፓርቲውን መፍረስ እና ገዢውን የብልጽግና ፓርቲ መቀላቀል በይፋ ተቃዉመዋል።
«እኔ ውሳኔውን እቃወማለሁ ፣ ስቃወምም ነበር ። ያው ክልሉ አብሮ መስራቱ የፓርቲው ሊቀመንበር ፣ ምክትል፣ ስልጣን ተሰጥቷቸው ነበር ። እና ከመላመድ የተነሳ የአብዛኛው ስራ አስፈጻሚ ግማሹ ከሀገር ውጭ ነው ያለው ፤ ግማሹም ለቋል እና ስልጣን ላይ ያሉትን አካል ደልለው ትክክለኛ ያልሆነ ጉባኤ አድርገው ፓርቲውን ትናንት አፍርሰዉታል። »
የህዝብ ጥያቄ መልስ ሳያጘን ፓርቲው መፍረስ አልነበረበትም የሚሉት ዶ/ር መብራቱ ዉሳኔውን ላለመቀበላቸው ምክንያትም ኾኗቸዋል።
«እኔ በዚህ ሰዓት ፓርቲ መፍረስ አለበት ብዬ አላምንም ። ቢያንስ የህዝቡን ፍላጎት፣ ጥቅም ፣ ጥያቄ መልስ ሳያገኝ የአመራሩ ጥቅም ስለተጠበቀ ብቻ ፓርቲ ወደ ማፍረስ መሄድ ለሃገራችን ፖለቲካ የሚሰጠው አንድምታ ጥሩ አይደለም የሚል እምነት ስላለኝ አፍርሶ መቀላቀሉን ብዙም አልተቀበልኩትም።»
ፓርቲው በውህደቱ የሚኖረው ሚና
ለመሆኑ ፓርቲው ከገዢው ፓርቲ ጋር ሲዋሃድ ሊኖረው ስለሚችል ሚና የተጠየቁት የፓርቲው ሊቀመንበርእንደሚሉት የፓርቲውን ህልውና ብሎም የህዝቡን ጥቅም እናስጠብቅበታለን ባሏቸው ጉዳዮች ላይ ከገዢው ፓርቲ ጋር የስምምነት ማዕቀፍ ማዘጋጀታቸውን ነው የሚገልጹት ።
«እሱን የስምምነት ማዕቀፍ አስቀምጠናል። ምን ሚና እንደሚኖረው ፤ አሁን ከዚህ በኋላ ጉባኤው አጠቃላይ ህጋዊ አካሄዶችን ከጨረሰ በኋላ ይፋ እናደርጋቸዋለን።ምን ምንድናቸው የሚለውን ሂደቱ ይድረስ ብለን ነው ያስቀመጥናቸው»
ትናንት ቡለን ውስጥ የተካሄደው የፓርቲው ጉባኤ ውሳኔውን በ280 ድጋፍ እና በሁለት ድምጸ ተአቅቦ ማጽደቁን አቶ አመንቲ ነግረዉናል ። ይህም ፓርቲው ህጋዊ መንገድንተከትሎ ውህደት ስለመፈ,ጸሙ እና የህዝቡን ጥቅም ለማስጠበቅ የተደረገ ነው ባይ ናቸው። የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባሉ ዶ/ር መብራቱ ግን በሊቀመንበሩ ሃሳብ አይስማሙም ።
«እኔ ደግሞ እንደዚያ ሳይሆን እርሳቸው የግል ጥቅማቸውን ስላስጠበቁ ስልጣን ስለተሰጣቸው፤ ብዙ ኢንቨስትመንቶች ውስጥም ስለገቡ ነውንጂ በርግጠኝነት የህዝብ ጥያቄ አንዳችም የተመለሰ የለም። ህዝቡ እያለቀ ባለበት በዚህ ሰዓት እንኳ የክልሉ መንግስት ህዝቡን መከላከል ባልቻለበት ፣ በጅምላ እየተጨፈጨፈ ባለበት ወቅት ለዚያ ህዝብ እታገላለሁ የሚልን ፓርቲ ማፍረስ በፍጹም በምንም አይነት መንገድ ተቀባይነት የለውም። »
አማራጭ መንገድ ፍለጋ
የፓርቲውን ህልውና ለማስቀጠል አማራጭ ይሆናሉ ያሏቸውን ርምጃዎች እንደሚወስዱም ነው የህዝብ ተወካይ ምክር ቤት አባሉ የነገሩን።
«ፓርቲን በማፍረስ ትግል ለማስቆም አስበው ነው ግን አይቆምም። ሌላም ፓርቲም ቢሆን እናደራጃለን የሚል ሃሳብ አለን። ወይም ደግሞ ከተደራጁ ፓርቲዎች ውስጥ ገብተን ትግል እናስቀጥላለን የሚል ነው በኔ በኩል ያለው» የቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሃሰን "ቦዴፓ ከክልሉ መንግሥት ጋር ለመሥራት ያሳለፈው ውሳኔ በተደመረ ዐቅም የህዝባችን ህይወት ለመቀየር የሚያስችል ነው" ማለታቸውን የክልሉ የመንግስት ኮሙኒኬሽን ቢሮ ዘግቧል። ፓርቲው ጠንካራ ድጋፍ እንደነበረው በሚነገርለት የቡለን ወረዳ ባለፈው ቅዳሜ ማለዳ ታጣቂዎች ባደረሱት ጥቃት ሴቶች እና ህጻናትን ጨምሮ ከሰላሳ በላይ ሰላማዊ ሰዎች መገደላቸው ይታወሳል።
ታምራት ዲንሳ
ነጋሽ መሐመድ
























