የሰው ሰራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጂ ለምን አሳሳቢ ሆነ?
Description
የሰው ሰራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጂ በፍጥነት እየተለወጠ እና እያደገ ያለ ቴክኖሎጂ ነው።ከእነዚህ እድገቶቹ መካከል፣ ጄኔሬቲቭ ኤአይ ከዚህ በፊት ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ በሰዎች የተሰሩ የሚመስሉ ምስሎችን ፣ ድምጾችን እና ቪዲዮችን የመፍጠር ችሎታው ጎልቶ ይታያል። ይህ የቴክኖሎጂ እድገት መልካም እድሎችን የሚፈጥር ቢሆንም በአንፃሩ ከፍተኛ አደጋዎችን የደቀነ መሆኑ ይነገራል።ይህን በሁለት በኩል የተሳለ ሰይፍነቱን የተረዱት የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር ፎልከር ቱርክ በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ስለቴክኖሎጂው ማስጠንቀቂያ ሰጥተዋል።
«ግዙፎቹ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች እንደ ሰውሰራሽ አስተውሎት ጀነሬቲቭ ኤአይ ያሉ አዳዳስ ቴክኖሎጂዎችን ሲያስተዋውቁ መጀመሪያ የሚጎዳው ሰብዓዊ መብት ሊሆን ይችላል።ጀነሬቲቭ ኤአይ ብዙ ተስፋ ሰጪ ነገሮች አሉት ግን የሚሰጠው ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ጥቅም ሊጭበረበር ሊዛባ እና ሊደናቀፍ ይችላል።» በማለት ገልፀዋል።
ቱርክ በተባበሩት መንግስታት ድርጅትየንግድ እና የሰብአዊ መብቶች ፎረም ላይ ባለፈው ሰኞ ባደረጉት ንግግር ጄኔሬቲቭ AI ቁጥጥር ካልተደረገበት፣ «ራንከንስታይን ሞንስተር» እየተባለ የሚጠራውን እና በሜሪ ሼሊ ልቦለድ ታሪክ ውስጥ የሚገኘውን እኩይ ወይም በተለምዶ «ጭራቅ» የምንለው አይነት ገፀባህሪ ሊሆን እንደሚችል አስጠንቅቀዋል።«አደጋው በበርካታ የሰብዓዊ መብቶች ላይ ይታያል። የግላዊነት ጥሰትን ጨምሮ የፖለቲካ ተሳትፎ፣ ሀሳብን በነፃነት የመግለጽ እና ስራ ግልፅ እና የወቅቱ አደጋ ነው።ያለ በቂ ጥበቃዎች እና መመሪያዎች የሰውሰራሽ አስተውሎት ስርዓቶች ወደ ዘመናዊ የፍራንከንስታይን ሞንስተር የመቀየር አቅም አላቸው።» በማለት የአደጋውን ስፋት ገልፀዋል።ቱርክ አይይዘውም ሰውሰራሽ አስተውሎት ተስፋ ሰጪ ቢሆንም ግዙፍ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች አላግባብ መጠቀማቸው መሰረታዊ የሰብአዊ መብቶችን ለመናድ እና በዓለም አቀፍ ደረጃ አለመረጋጋትን እንዳይፈጥር ያሰጋል ብለዋል።የእሳቸው መልእክት -የቴክኖሎጂ ፈጠራ ከፖሊሲ፣ ከሥነ-ምግባር እና ከተጠያቂነት የላቀ መሆኑ በአለምአቀፍ አስተዳደር ውስጥ የፈጠረውን ሰፊ ስጋት ያንጸባርቃል።ሰውሰራሽ አስተውሎት ከጊዜ ወደ ጊዜ በፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ስርዓቶች ውስጥ እየተዋሃደ ሲሄድ፣ በዓለም ላይ ትልቅ ስጋት እንደሚያስከትል ገልፀዋል።
ቴክኖሎጂው ለምን አሳሳቢ ሆነ?
የቱርክን ማስጠንቀቂያ አስፈላጊነት ስንመለከት ጀነሬቲቭ ኤአይ ምን እንደሆነ መረዳት በጣም አስፈላጊ ነው። ይህ ቴክኖሎጂ ከመረጃ ቋት የሚያገኘውን ግዙፍ የውሂብ ስብስብ በመጠቀም አዳዲስ የድምፅ ፣የምስል፣የፅሁፍ እና የቪዲዮ ይዘቶችን ያመነጫል።በዚህም ከመዝናኛ እና ከትምህርት እስከ የንግድ ሥራ ትንተና እና ሳይንሳዊ ምርምር ድረስ ያሉ መስኮች ላይ አብዮት ፈጥሯል። ነገር ግን በርካታ ስጋቶችንም ደቅኗል።ከነዚህም መካከል የሳይበር ደህንነት እና የኤአይ ደህንነት ፖሊሲ ባለሙያው ጋዜጠኛ አበበ ፈለቀ ቀደም ሲል እንደገለፀው የተሳሳተ መረጃ መስጠት አንዱ ነው። በሌላ በኩል በሰውሰራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጂ ለተፈጠሩ ይዘቶች ግብዓት የሚሆኑ ግላዊ መረጃዎችን እንዴት እንደሚጠቀሙ ወይም እንደሚደግሙ ግልጽነት ላይም ጥያቄዎችን ያስነሳል።ከመረጃ አሰባሰብ ባሻገር፣ በ AI የተፈጠሩ ጥልቅ ሀሰተኛ ይዘቶች በእውነተኛው እና በሀሰት በተፈበረከው ይዘት መካከል ያለውን ድንበር በማደብዘዝ ለመለየት አስቸጋሪ ያደርጋል።
አደጋ በሰብአዊ መብቶች ላይ
የተቀናበረ ድምፅ ወይም ቪዲዮ ግለሰቦችን ለማጥላላት፣ ታዋቂ ሰዎችን ስምለማጥፋት ወይም ሀሰተኛ የፖለቲካ ትርክቶችን ለመፃፍ ሊውል ይችላል።የጄኔሬቲቭ AI ስርዓቶች በመረጃ ላይ የተመሰረተ ሲሆን፤ ብዙውን ጊዜ ያለ ግልጽ ፍቃድ ከበይነመረቡ ይሰረዛሉ ።የግለሰቦችን የግል መረጃም ያለግለሰቦች ፈቃድ ለስልጠና ግብዓት ያደርጋሉ። ይህም በግለሰቦች መብት ላይ ጥያቄ ያስነሳል።
ቴክኖሎጂው ሰብዓዊ መብቶች ላይ ጉዳት ያደርሳል የሚለው የኮሚሽነር ፎልከር ቱርክ ማስጠንቀቂያ ይህንን የቴክኖሎጅውን ተደጋጋሚ አካሄዶች ያጎላል።የተሳሳተ መረጃን ከሚያጎሉት የማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ስልተ ቀመሮች እስከ የዲጂታል የግላዊነት ደንቦችን የሚቀርፁ የዉሂብ ማመንጨት ስራዎች ድረስ ፣ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች በማህበረሰቡ ላይ ያለውን ተፅዕኖ ሳይገመግሙ የቴክኖሎጂ ስርዓቶችን በስፋት ዘርግተዋል።ከዚህ አንፃር የመረጃ ስርቆት ሌላው ችግር መሆኑን የሳይበር ደህንነት ከፍተኛ ባለሙያው አቶ ብሩክ ወርቁ ከዚህ ቀደም ገልፀዋል።
የፖለቲካ ተሳትፎን የመገደብ እና ነፃ ሀሳብን የማፈን ስጋት
የፖለቲካ ፕሮፓጋንዳ መፍጠር፣የተዛባ መረጃን በመሰራጨት ነፃ ምርጫን ሊያዳክሙ፣ የሕዝብን አስተያየት ባልሆነ መንገድ ሊቀርጹ እና ለመለየት ወይም ለማስተካከል አስቸጋሪ በሆኑ መንገዶች የዴሞክራሲያዊ ገጽታን ሊለውጡ ይችላሉ።ሀሳብን በነፃነት ከመግለፅ አንጻር፤ AI ሀሳብን የመግለፅ ነፃነት የማጎልበቱን ያህል ሊያፍንም ይችላል። ሰውሰራሽ የይዘት ቁጥጥር ማድረጊያ ስልተ ቀመሮች ህጋዊ ፖለቲካዊ ወይም ጥበባዊ ንግግርን ሳንሱር ሊያደርጉ ይችላሉ። መንግስታት የፖለቲካ ተቃዋሚዎችን፣ የመብት ተሟጋቾችን ለመለየት ወይም ተቃዋሚዎችን ዝም ለማሰኘት ሰውሰራሽ አስተውሎትን ሊጠቀሙ ይችላሉ። ስልጣን በጥቂት ኩባንያዎች ወይም በመንግስት ተዋናዮች እጅ ውስጥ ሲከማች ደግሞ ኮሚሽነሩ እንደገለፁት የጉዳቱ መጠን ጉዳቱ ይጨምራል።
ቴክኖሎጂው ገንቢዎቹ ከሚከታተሉት በበለጠ ፍጥነት በፍጥነት የሚለዋወጥ በመሆኑም ባልተጠበቀቁ መንገዶችም ሊሰራ ያልተጠበቁ አድልዎዎችን ሊያዳብር ይችላል።ሆን ተብሎ ወይም በተንኮል አዘል ተዋናዮች ለጎጂ ዓላማዎች ጥቅም ላይ ሊውል ይችላል።ያም ሆኖ የሶፍትዌር ባለሙያው አቶ ዳዊት ዓለሙ ቀደም ሲል እንደገለፁት የቴክኖሎጂ ኩባንያዎቹ እንኳ እነዚህን ስህተቶች ማስተካከል ወይንም ሂደቱን መግለፅ አይችሉም።
የ«ፍራንከንሽታይን ጭራቅ» ምሳሌ የቁጥጥር ማስጠንቀቂያ
ከዚህ አንፃር የፎልከር ቱርክ የ "ዘመናዊው የፍራንከንስቴይን ጭራቅ" ምሳሌ ከልቦለድ እኩይ ገፀባህሪ በላይ ነው። በቴክኖሎጂ ፈጠራ ታሪክ ውስጥ ሰዎች ሙሉ በሙሉ የማይረዷቸውን ወይም የማይቆጣጠሯቸውን ስርዓቶች መፍጠራቸውን የሚያሳይ ጥልቅ ስጋት ነው።በሜሪ ሼሊ ልብ ወለድ ውስጥ፣ ያለው ጭራቅ ሲፈጠር ክፉ አልነበረም።አስከፊነቱ የመጣው ስለተተወ፤ በተሳሳተ መንገድ ስለተረዱት እና ቁጥጥር ስላልተደረገበት ነው። ከጄኔሬቲቭ AI ጋር ያለው ተመሳስሎም ይህ ነው።ቱርክ ለቴክኖሎጂ እምቅ አቅም እውቅና በመስጠት ጄኔሬቲቭ AIን ለፈጠራ፣ ችግር ፈቺ እና ለዓለምአቀፋዊ እድገት ትልቅ ተስፋ ያለው መሆኑን ገልፀዋል።ነገር ግን በጥቂት ግዙፍ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች ባለቤትነት የተያዙ እናየመንግስታት ቁጥጥር አነስተኛ በሆነበት ሁኔታ- ጄኔሬቲቭ AI ለጋራ እድገት ሳይሆን ለጥቂቶች መጠቀሚያ እና ለብዝበዛ ሊውል ይችላል የሚለውም ሌላው በዚህ ቴክኖሎጂ የሚነሳ ስጋት ነው።
የዓለም አቀፍ ደንብ እና የጋራ እርምጃ አስፈላጊነት
ስለሆነም ዓለም አሁን እርምጃ ካልወሰደ በስተቀር፣ AI ከቁጥጥር ውጭ የሆነ ኃይል ሊሆን እንደሚችል ቱርክ ጠቁመዋል።በዲሞክራሲያዊ እሴቶች ወይም በሰብአዊ መብቶች ሳይሆን በኩባንያዎች ፍላጎቶች ወይም በጂኦፖሊቲካዊ ኃይሎች ትግል የተቀረጸ ይሆናል።ያከመሆኑ በፊት የጋራ እርምጃ እንደሚያስፈልግ ገልፀዋል።«ዛሬዎቹ ስጋቶች ወደ ተጨባጭ ጉዳት ሊቀየሩ ይችላሉ። በአዳዲስ ቴክኖሎጂዎች ላይ ያለውን ተስፋ የሚያፈርሱ እና ሊተነብዩ የማይችሉ መዘዞችን ሊያስከትሉ ይችላሉ።መንግስታት እንዲህ ያለውን ውጤት ለመከላከል አንድ ላይ የመተባበር ሃላፊነት አለባቸው።» ብለዋል።የቴክኖሎጂ ኩባንያዎችም የበኩላቸውን እንዲያደርጉ አሳስበዋል።«ባንያዎችም ቢሆን የተለዬ መንገድ መምረጥ አይችሉም።አንዳንዶች ይህን አድርገዋል።ዲጅታል ቴክኖሎጂዎች የሰብዓዊ መብቶችን የማሻሻል እና የህዝብ አገልግሎቶችን ጥሩ የማድረግ ዕድሎችን ማየት ይችላሉ።» ሲሉ ተናግረዋል።
የፎልከር ቱርክ ማስጠንቀቂያ ሰውሰራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጂን ያለመቀበል ሳይሆን የሚገባውን ትኩረት ሰጥቶ ቁጥጥር እና የስነምግባር ደንብን ማዘጋጄትን የሚጠይቅ ነው።ምክንያቱም ሰውሰራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጂ ተጽእኖዎች በሰዎች ምርጫ ላይ የተመሰረተ ነው።.ያለ አርቆ አስተዋይነት ከተጠቀምንበት፣ እውነትን ሊያዛባ፣ ዲሞክራሲን ሊያናጋ፣ መብቶችን ሊያዳክም እና እኩልነትን ሊያጠፋ ይችላል። በደንብ የታሰበበት ደንብ እና ዓለም አቀፋዊ ትብብር ካለ ግን በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ በጎ ለውጥ ከሚያመጡ ኃይሎች አንዱ ሊሆን ይችላል። የሶፍትዌር ባለሙያው አቶ ዳዊት አለሙ ይህንኑ ሀሳብ ያጠናክራሉ።
ከዚህ አንፃር የሰብዓዊ መብት ኮሚሽነሩ ያቀረቡት ምርጫው ሁለት ነው። ገዢ ፖሊሲዎች እና የስነምግባር ደንቦችን በማዘጋጄት ቴክኖሎጂውን መጠቀም አልያም ከሰዎች ቁጥጥር ውጭ የሆነ "የፍራንከንስታይን ጭራቅ"እንዲሆን መፍቀድ።የሰው ልጅ አሁን መንታ መንገድ ላይ ቆሟል።እናም መጪዎቹ ዓመታት ጀነሬቲቭ AI የእድገት እና የመሻሻል መሳሪያ አልያም ከኛ ቁጥጥር ውጭ የሆነ "የፍራንከንስታይን ጭራቅ" መሆን አለመሆኑን ይወስናሉ።እናም ይህንን ቴክኖሎጂ ሰዎችን የሚያገለግል፣ ሰብአዊ መብቶችን የሚያጠናክር እንዲሁም ለእኩልነት እና ለፍትሃዊነት የበለጠ አስተዋጾ እንዲያደርግ ዓለም በስነምግባር የሚመራ የጋራ እርምጃ መውሰድ እንዳለበት ባለሙያዎች ያሳስባሉ።
ፀሐይ ጫኔ
ነጋሽ መሀመድ























