ትኩረት በአፍሪካ፤ የማቻር ፍርድ ቤት መቅረብ፤ ኡጋንዳ 40 ዓመታት በዩዌሪ ሙሰቬኒ ሥር
Description
የማቻር ፍርድ ቤት መቅረብ የደቡብ ሱዳንን የፖለቲካ ቀውስና የጎሳ መከፋፈል
ከሱዳን ለመነጠል ሲዋጉ የነበሩት ደቡብ ሱዳናውያን እንደ ጎርጎሮሳውያኑ አቆጣጠር ሐምሌ 9 ቀን 2011 ዓም ነጻ ሐገር ቢመሰርቱም የነጻነቱ ትሩፋት ግን የእርስ በእርስ ጦርነት መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ። የነጻነቱ ፈንጠዝያና ደስታው ከሁለት ዓመታት በላይ መዝለል አልተቻለውም። በሪክ ማቻር የኑዌር ጎሳዎች እና በሳላቫ ኪር ዲንካ ታማኝ ደጋፊዎች መካከል ግጭቶች እና ጦርነቶች በመፋፋሙ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩትን ሞተዋል፤ በሚልዮን የሚቆጠሩት ደግሞ ተፈናቅለዋል አልያም ሐገር ጥለው ተሰደዋል። የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በየጊዜው በሚያወጣቸው መረጃዎች እንደሚያመላክቱት የተሰደዱት እና የተፈናቀሉት ለምግብ እጥረት ተጋልጠዋል፤ በቂ ሕክምና ንጹሕ የመጠጥ ውሃና መጠለያ አያገኙም።
እንደ ጎርጎሮሳውያኑ አቆጣጠር ነሐሴ 2015 ዓ.ም ፕረዚደንት ሳልቫ ኪርና ተቀዳሚ ምክትል ፕረዚደንት ሪክ ማቻርየሰላም ስምምነት ከተፈራረሙ በኋላ በሚያዚያ 2016 ጥምር መንግስት ለመመስረት ተችሎ ነበር። ይሁንና ከሦስት ወራት በኋላ በሐምሌ ወር ጁባ ውስጥ የኪርና የማቻር ኃይሎች ተመልሰው ወደ ውግያ መመለሳቸውን መረጃዎች ያመላክታሉ። የአፍሪካ ሕብረትን ጨምሮ በርካታ ባለድርሻ አካላት ባደረጉት ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶች እንደ ጎርጎሮሳውያኑ አቆጣጠር በመስከረም 2018 የሰላም ስምምነት ተፈረመ። ስምምነቱን መሰረት በማድረግ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ አቆጣጠር በግንቦት 2019 የሽግግር መንግስት በመመስረት በታኅሳስ 2022 ምርጫ ይካሄዳል ተብሎ ሲጠበቅ በየካቲት 2020 ሪክ ማቻር ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዝዳንት የሆኑበት የሽግግር መንግሥት ቢመሰረትም በፕረዚደንቱና ምክት ፕረዚደንቱ መካከል በስልጣን ድልድል በተፈጠረ አለመግባባት ውዝግቡ እንደቀጠለ ነው። ውዝግቡ ተካሮ የሪክ ማቻር ጦር በመንግት ወታደሮች ላይ ወሰደው በተባለ ጥቃት ውዝግቡ ወደ ከፋ ደረጃ እንዳደረሰው ይነገራል። ለጥቃቱ ተጠያቂ ናቸው ተብለው የተጠረጠሩት ሪክ ማቻር እንደ ጎርጎሮሳውያኑ አቆጣጠር በመጋቢት ወር 2025 በቁጥጥር ሥር ውለው በአለፈው ሰኞ ፍርድቤት ቀርበዋል።
የሪክ ማቻር ፍርድቤት መቅረብና የጎሳ ግጭት ስጋት
የደቡብ ሱዳን ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዚዳንት ሪክ ማቻር ፍርድ ቤት መቅረባቸውንበደቡብ ሱዳን ዳግም ግጭት እንዳይነሳ ስጋት አሳድሯል። በቋፍ ላይ የነበረውን የአገሪቱን ሰላምና የአንድነት መንግሥት አደጋ ላይ እንደጣለም ይነገራል። ከአለፈው መጋቢት ወር ጀምሮ በእስር ላይ የሚገኙት ማቻር፣ የፔትሮሊየም ሚኒስትር ፑት ካንግ ቾልን ጨምሮ ከ20 ተከሳሾች ጋር ሰኞ ዕለት በዋና ከተማዋ ጁባ ልዩ ፍርድ ቤት ቀርበዋል ።
ተከሳሾቹ ፍርድቤት የቀረቡት በዚህ ዓመት መጀመሪያ ላይ በናስር ግዛት ሚሊሺያዎቻቸውን በማሰማራት ፈጸሙት በተባለው አሰቃቂ ግድያ፣ በሰብአዊነት ላይ የተፈጸመ ወንጀልና የአገር ክህደት ተጠርጥረው ነው።
የስቪክ ማሕበረሰብ አባላት ጥሪ
በደቡብ ሱዳን የሰብዓዊ መብት ጥበቃ ሕብረት የሰብአዊ መብት ተከራካሪ የሆኑት ኦማራ ጆሴፍ ለዶይቸቨለ እንደገለጹት የማቻር ፍርድቤት መቅረብ አዎንታዊም ሆነ አሉታዊ አንድምታ አለው ብለዋል። ይሁንና የደቡብ ሱዳን መንግስት ነጻ የመገናኛ ብዙሃን ጋዜጠኞች ችሎቱን ተከታትለው እንዳይዘግቡ በመንግስት መከልከላቸውን ተችቷል።
«የእሳቸው ለፍርድ መቅረብ ደቡብ ሱዳንም ተጠያቂነትን ልታሰፍን እንደምትችል ማሳያ ነው ።ከሕግ ጋር የሚጋጭ ማንኛውም ሰው ተጠያቂ ሊሆን ይችላል ። ዓለም አቀፍ ተዋንያንም ጫና የሚያሳድሩበት ወቅት አሁን ነው። ምክንያቱም በዚህ ችሎት ምን እየተከናወነ እንደሆነ ዓለምአቀፉ ማሕበረሰብ ማወቅ አለበት። ችሎቱን መከታተልን ለምን የመንግስት መገናኛ ብዙሐን ብቻ ይፈቀዳል? ለምን ነጻ መገናኛ ብዙሃን ችሎቱን እንዳይከታተሉ ተከለከሉ? »
ታዛቢዎች እንዲህ ዓይነቶቹ እገዳዎች የፍርድ ሂደቱ በፖለቲካዊ ግፊት የሚደረግና ፍትሐዊ ነው ብሎ ለማመንም እንደሚያስቸግር ያስጠነቅቃሉ ።
የፍርድ ሂደቱ በማቻር የኑዌር ጎሳዎች እና በኪር ዲንካ ታማኝ ደጋፊዎች መካከል የዘውግ መከፋፈል አንግሷል ። የሲቪል ማህበረሰብ ተሟጋቿ ታቢታ ንያንቲን ለዶይቸቨለ እንደገለጹት የደቡብ ሱዳን መሪዎች ለአገር አንድነት ቅድሚያ መስጠት አለባቸው ።
«በዚህች አገር ብዙ ጎሣዎች አሉን። መሪዎቹም ከተለያዩ ጎሳዎች የመጡ ናቸው። አስተሳሰባቸው ካልተለወጠና አስፈላጊውን እርምጃ ካልወሰዱ በጎረቤታችን ኬንያ እንዳጋጠመው በደቡብ ሱዳንም የሚያጋጥም ይሆናል።»
የማቻር ለፍርድ መቅረብና ሰበቡ
የሰላም ስምምነቱና የጥምር መንግስት እንዲሁም የሐገሪቱ ብሔራዊ ምርጫ አጀንዳዎች የዲንካ ጎሳ አባላትን ዒላማ አደረገ የተባለውን በቦር ከተካሄደው ጭፍጨፋ በኋላ በሁለቱ መሪዎች መካከል አለመተማመንን ይበልጥ እንዲጠናከር አድርጓል ። ከሁለቱም መሪዎች አልፎም የጎሳ ግጭቱን ይበልጥ እንዳይስፋፋ ተሰግቷል። ሳልቫኪር ለጭፍጨፋው ማቻርን ተጠያቂ ያደረጉ ሲሆን በሰብአዊነት ላይ የተፈጸመ ወንጀል፤ እንዲሁም ጭካኔ የተሞላበት ግድያን መፈጸም የሚሉ ተደራራቢ ክሶች በሪክ ማቻው ላይ ዶሴ ተከፍቶባቸዋል።
ሁለቱም መሪዎች ቀደም ሲል በአንድ መንግሥት ውስጥ አብረው ቢያገለግሉም ተንታኞች ግን በመካከላቸው ያለው ግንኙነት ልባዊ እንዳልነበረ ይናገራሉ ። በሐገራት ቀውሶች ላይ ጥናትና ትንታኔ የሚሰጠው የዓለም አቀፉ ቀውስ ቡድን ከፍተኛ ተንታኝ የሆኑት ዳንኤል አኬች ለአሶሼትድ ፕሬስ እንደገለጹት በማቻር ላይ የቀረበው የወንጀል ክስ "የፖለቲካ የሥልጣን ሽኩቻ ሰበብ" ይመስላል ብሏል።
በደቡብ ሱዳን ፕሬዝዳንታዊ ምርጫዎች በተደጋጋሚ ሲራዘሙ የቆዩ ሲሆን አሁን የተፈጠረው ቀውስም ወደፊት በጎርጎሮሳውያኑ አቆጣጠር በ2026 ይካሄዳል የተባለውን ምርጫ የሚያደናቅፍና ሐገሪቱን ወደትርምስ የሚያስገባ እንደሆነ ተንታኖች ያስጠነቅቃሉ።
እንደ ጎርጎሮሳውያኑ አቆጣጠር የ2018 የሰላም ስምምነት ከ400,000 በላይ ሰዎችን ለሞት 7 ሚልዮን ሕዝብ ደግሞ ለረሐብ አደጋ የዳረገውን የአምስት ዓመታት የእርስ በርስ ጦርነት እንዲያበቃ አድርጎ የነበረ ቢሆንም የአንድነት መንግሥቱ በመበታተኑ ላይ የማቻር ፍርድ ቤት መቅረብ ተጨምሮበት ደቡብ ሱዳንን እንደገና ወደ ግጭት ሊመልሳት ይችላል እየተባለ ነው። ለዛም ነው የሪክ ማቻር የፍርድ ሂደት የእሳቸውና እና የተባባሪዎቻቸው ብቻ ሳይሆን የደቡብ ሱዳን የወደፊት እጣ ፈንታን የሚወስን ነው የሚባለው።
ኡጋንዳ 40 ዓመታት በዩዌሪ ሙሰቬኒ ሥር
ከ40 ዓመት ዕድሜ በታች ለሆኑ በሚሊዮን ለሚቆጠሩ ኡጋንዳውያን እስከ ዛሬ የሚያውቁት ፕሬዚዳንት ዮዌሪ ሙሴቬኒ ብቻ ናቸው ። እናም ይህ በቅርቡም ይለወጣል ተብሎ አይታሰብም። ምክንያቱም የኡጋንዳ የምርጫ ኮሚሽን በመጪው የካቲት ወር ለሚካሄደውፕሬዝዳንታዊ ምርጫ እጩዎችን የመጨረሻ ዝርዝር ካረጋገጠ በኋላ ሙሴቬኒ ከዕጩ ተወዳዳሪዎች መካከል አንዱ በመሆናቸው።
የ81 ዓመቱ ፕረዚደንት ዩዌሪ ሙሴቬኒ ለመጀመሪያ ጊዜ ሥልጣን ላይ የወጡት እንደ ጎርጎሮሳውያኑ አቆጣጠር በ1986 ሚልተን ኦቦቴን ከሥልጣን ያባረረውን የታጠቀ ዓመፅ ተከትሎ ሲሆን በዓለም ላይ ለረጅም ጊዜ ከቆዩት መሪዎች አንዱ ሆኗል ።
የፕረዚደንቱ ስልጣን ዘመን በምስጋናም በትችትም የተሞላ ነው ። አመስጋኝ ደጋፊዎቻቸው እንደሚሉት ሙሰቬኒ ለሐገሪቱ መረጋጋትና ዕድገትን አምጥተዋል። ተቺዎች ግን ኡጋንዳ ከጊዜ ወደ ጊዜ ዲሞክራሲያዊ ሂደቷ እየተሸረሸረ፤ የሰብዓዊ መብት ጥሰትና ሙስና እየተስፋፋ ነው ይላሉ ።
የመረጋጋት ውርስ
«ሙሴቬኒ በአገራችን አስደናቂ ለውጥ ያመጣ ሲሆን በተለይም እውነተኛ ሰላምና መረጋጋት ታይቷል» ይላሉ የማህበራዊ ሥራ ፈጠራ ባለሙያና ፖለቲከኛ የሆኑት አግነስ አቲም አፔያ። ይህ መረጋጋት የኢኮኖሚ ዕድገትን እንዳፋጠነው በማከል።
«አዎን ፣ ፕሬዚዳንቱ በአገራችን አስደናቂ ለውጥ አድርገዋል በሚለው ሐሳብ መስማማት አለብን። በሐገሪቱ በተለይም ሰላምና መረጋጋት አለ። ስለሰላም ስናገር ትርጉሙ ምን እንደሆነ ጠንቅቄ እረዳለሁ። እንደሚመስለኝ ፕረዚደንቱ ትኩረት ካደረጉባቸው መስኮች አንዱ ይህ ይመስለኛል። ይህ ደግሞ በሐገሪቱ ለተመዘገቡ ልማቶችና ለውጦች ያነቃቃውም ሰላሙ ይመስለኛል። ምክንያቱም ሰላምና መረጋጋት ከሌለ መንገድ መስራት አትችልም፤ የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማትን ማስፋፋት አትችልም። እንደሚመስለኝ በዚህ መስክ ፕረዚደንቱ ላስመዘገቡት ውጤት በእውነት! በእውነት! ልናጨበጭብላቸው ይገባል።
ይሁንእና በአሁኑ ጊዜ ግብርናው እየተቀዛቀዘ እንደሆነ አይተናል። የተለያዩ ለቀለብ የሚሆኑ ሰብሎች ከሌሎች ሐገራት እያስመጣን ነው። በአጠቃላይ ሲታይ ኢኮኖሚው በማነቃቃት ፕረዚደንቱ ጥሩ ውጤት አስመዝግበዋል። በተለይም የሰደድ ንግድ፣ አገልግሎት ሰጪ ተቋማትን ማስፋፋት፣በትራንስፖርት፣ በቱሪዝም ዘርፍም እንዲሁ በጣም ጥሩ ሥራዎች ሰርቷል። እንደሚመስለኝ እነዚህ የኤኮኖሚ ዕድገትን ለማስመዝገብ ወሳኝ ሥራዎች ናቸው።»
ሙሴቬኒ ሥልጣን ከያዙ በኋላ የተወለዱት ሮበርት ኦንያንጎ በቀጣዩ ምርጫ ድምፅ ለመስጠት በጉጉት እየተጠባበቁ ነው ። የፕሬዚዳንቱን ውርስ በጥሩ ሁኔታ ይመለከቱታል። እሳቸው ለዶይቸቨለ በሰጡት አስተያየት «ከዚህ መንግሥት ጋር አብረን አድገናል። የምናወራው ስላየነው መልካም ጎን ብቻ ነው» ባይ ናቸው።
« መልካም! የመጀመሪያውና ዋናው ጉዳይ እንደኛ ትውልድ፤ ስለ40ዎቹ የፕሬዘዳንት ዩዌሪ ሙሴቪኒ የሥልጣን አመታት ብዙ የምንናገረው ነገር የለም። ምክንያቱም ያወቅነው መንግስት ይህ ብቻ ነው ። እኛ የተወለድነውም ያደግነውም በዚህ መንግሥት ውስጥ ነው። እኛ የምናውቀው ይህንኑ መንግሥት ነው ። ስለሆነም በዮዌሪ ሙሴቬኒ መንግሥት ውስጥ ስላየነው መልካም ጎን ብቻ ነው የምናወራው። እርግጥ ነው ፣የሙሴቨኒ መንግስት የሚወቀሰው በሰብአዊ መብቶች ጉዳይ ነው ። ኡጋንዳውያን ሕገ መንግሥቱ ባስቀመጠው መሠረት ነፃነታቸውን እንዲያገኙ ለማድረግ ብዙ ፕሮግራሞች አሉ። እርግጥ ሰብዓዊ መብታችን ተጥሷል ብለው የሚከሱ ሰዎች አሉ። ይህ በፖለቲከኞች በኩል ይበልጥ አስፈላጊ ነው ። ከፖለቲካ ወገን ያልሆኑ ሰዎች ግን ሐሳብን የመግለጽ ነፃነታቸውን ሲጎናጸፉ እንመለከታለን።»
በዴሞክራሲ ላይ ያሉ ህፀፆች
በኡጋንዳ ተመዘገበ ከሚባለው የኢኮኖሚ ዕድገት ባሻገር በዴሞክራሲ በኩል ያሉ ችግሮች መሰረታዊ እንደሆኑ ብዙዎች ያነሳሉ። የኡጋንዳ ሕገመንግስታዊ መንግስት ጥበቃ ማዕከል ዋና ዳይሬክተር የሆኑት ዶክተር ሳራ ብሬተ ለዶይቸቨለ በሰጡት አስተያየት በኡጋንዳ የዴሞክራሲ እሴቶች እየተሸረሸሩ እንደሆነ ያስረዳሉ።
«በሕግ የበላይነትና ዴሞክራሲ ጠቋሚ ዓለም አቀፍ መመዘኛዎች ከ148 ሐገሮች 121ኛ ደረጃ ላይ ነን። የሕግ የበላይነት ደግሞ የዴሞክራሲ የመአዝን ድንጋይ ነው። የዴሞክራሲ ተቋማትን ነጻነትን ከማስጠበቁም በላይ በሕግ አውጪውና ሕግ ተርጓሚው መካከል እንደመቆጣጠሪያና የሚዛን ልኬት ነው። በመሆኑም ተጠያቂነትን ያሰፍናል። በዚህ ረገድ ከወደቅን ኡጋንዳ እያደገች ነው አደለም ? የሚል ጥያቄ ያስነሳል።
ሌላ የዴሞክራሲ እሴቶችን ብንመለከት ተአማኒ፣ ነጻና ፍትሃዊ ምርጫ ነው። የምርጫ ሂደቶቻችን ብንመለከት በገንዘብና የፀጥታ ሃይሎች ፖለቲካውን ስለተቆጣጠሩት ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሽቆለቆለ ይገኛል። የ2021 ምርጫን እንደምሳሌ ብንወስድ በዓመፅ የተሞላ ነበር። ይህ የምርጫ፤የዴሞክራሲ ሂደቶቻችን ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሽቆለቆለ ለመሆኑ ማሳያ ነው።
ስለመራጮች ትምህርት ብናነሳም ያለ በቂ የመራጮች የአመራረጥ ትምህርት መጪው ምርጫምን መጠበቅ እንዳለብህ መገመት አያዳግትም። በእርግጥ በኡጋንዳ ያለው ሥር የሰደደ ሙስናም አንዱ ተግዳሮት ነው። በየአመቱ ወደ 10 ትሪልዮን ሽልንግ በሙስና ይዘረፋል። በዓመት ከግብር 32 ትሪልዮን ሽልንግ ሰብስበህ ወደ 10 ትሪልዮን ሽልንግ በሙስና የሚጠፋ ከሆነ በኡጋንዳ ያለውን ዴሞክራሲ ማሳያ ነው።»
በዩጋንዳ ዩኒቨርስቲ ፕሮፌሰር ማቢነ ፕሬዚደንት ዩዎሪ ሙሰቬኒ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ አቆጣጠር በ1986 ወደ ስልጣን ከመጡ ወዲህ የዴሞክራሲ ሂደቱ መሻሻልን እንዳሳየ እውቅና ይሰጣሉ። ይሁንና አንዳንድ መንግስታዊ ተቋማት የሰብአዊ መብት እንደሚረግጡና የዜጎች ነጻነትን እንደማያከብሩ ግን አልሸሸጉም። በዚህ አይነት ሂደት ቀጣዩ ዓመት የሚካሄደው ምርጫ ዩጋንዳ በዴሞክራሲ ባለህበት ትረግጣለች ወይስ መሻሻል ታመጣለች የሚለውን ተጠባቂ አድርጎታል።
ዮሃንስ ገብረእግዚአብሄር
ታምራት ዲንሳ።