DiscoverDW | Amharic - Newsጀርመን ብሄራዊ ውትድርና አገልግሎት ምልመላ ልትጀምር ነው
ጀርመን ብሄራዊ ውትድርና አገልግሎት ምልመላ ልትጀምር ነው

ጀርመን ብሄራዊ ውትድርና አገልግሎት ምልመላ ልትጀምር ነው

Update: 2025-11-14
Share

Description

ከወራት የዘለቀው ክርክር በኋላ የጀርመን ጥምር መንግስት የወታደሮችን ቁጥር ለመጨመር አዲስ ዘዴ ለመንደፍ ተስማምቷል። ቡንድስዌህር እየተባለ የሚጠራው የጀርመን ጦር በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ተጨማሪ ወታደሮች እንደሚያስፈልገው ገልጿል።ለዚህም ብሄራዊ ውትድርና አገልግሎት ምልመላ ለመጀመር ተስማምቷል።ምልመላው በፈቃደንነት የተመሰረተ ነው ተብሏል።

በመጭው ታህሳስ ወር በጀርመን ፓርላማ የሚቀርበው ረቂቅ ህግ "አዲሱ ወታደራዊ አገልግሎት መጀመሪያ ላይ በፈቃደኝነት ላይ የተመሰረተ ነው" የሚለው ቁልፍ ዓረፍተ ነገር ነው። ወደፊት ግን ለሁሉም 18 አመት የሆናቸው ወንዶች የግዴታ የአካል ብቃት ምዘናዎች ይኖራሉ ተብሏል።

ከመሃል ግራው ሶሻል ዴሞክራቲክ ፓርቲ (ኤስፒዲ) አባሉ የመከላከያ ሚኒስትሩ ቦሪስ ፒስቶሪየስ አዲሱን የበጎ ፈቃድ ወታደራዊ አገልግሎት ከቀድሞው የግዳጅ አገልግሎት በተሻለ ሁኔታ እና ደሞዝ በመጭው ጥር ወር መጀመሪያ ላይ ለመጀመር መታቀዱን ገልፀዋል። የወግ አጥባቂው የክርስቲያን ዲሞክራቲክ ህብረት (ሲዲዩ) እና የባቫሪያን እህት ፓርቲ የክርስቲያን ሶሻል ዩኒየን (CSU) ፖለቲከኞች ግን፤ ይህ ትልቅ ግብ ሊሳካ የሚችለው ወደ አስገዳጅ የውትድርና አገልግሎት ሀገሪቱ ከተመለሰች ብቻ ነው ሲሉ ተከራክረዋል።ጉዳዩ በጀርመን ማኅበረሰብ ውስጥም ውዝግብ አስነስቷል።ከበርሊን የዶቼ ቬለ የፖለቲካ ዘጋቢ ኒና ሃዘ እንደምትለው ርምጃው ጀርመንን አሁን ካለው የጅኦ ፖለቲካ እውነታ ጋር ለማስማማት ነው።



«ሁሉም ሰው ጉዳዩን አዲስ ግኝት አድርጎ ያወራዋል ግን የጀርመን ጦር ፓርላሚንታዊ የሚባል ነው።እና ብዙ ሰዎች በዚህ ላይ እየተወያዩ ነው። በጉዳዩ ላይ በጀርመን ማኅበረሰብ መካከል የከረረ አበር።የጀርመን ጦር በሚታየው የጆኦ ፖለቲካ ምክንያት በፍጥነት ማደግ እንዳለበት ግንዛቤ የለም። እየተካሄደ ያለው የራሺያ ዩክሬን ጦርነት አለ። ስለዚህ ጀርመን ላለመዋጋት መታገል መቻል አለባት።»ስትል ገልፃለች።

የሶሻል ዴሞክራት ፓርቲ ግን ወደ አስገዳጅ የውትድርና አገልግሎት መመለሱን በጥብቅ ውድቅ አድርጓል። ነገር አሁን ፓርቲዎቹ ስምምነት ላይ ደርሰዋል።የCDU/CSU የፓርላማ ቡድን ስምምነቱን አድንቋል።

የጀርመን መከላከያ ሚንስትሩ ፒስቶሪየስ ፤ዓላማቸው በ2026 ዓ/ም 20,000 አዳዲስ በጎ ፈቃደኞችን መቅጠር ነውየጀርመን ጦር በአሁኑ ጊዜ 182,000 ወታደሮች ያሉት ሲሆን፤ የኔቶ መስፈርቶችን ለማሟላት ግን በጎርጎሪያኑ 2035 ቢያንስ 260,000 ወታደሮችን ይፈልጋል።የመንግስት አካላት የጀርመንን የመከላከያ ፍላጎት ለማርካት በቂ ፈቃደኞችን መቅጠር ይችሉ እንደሆነ ግን ጥርጣሬዎች አሉ። ኒና ሃዘ ጥርጣሬውን ትጋራለች።

«የመከላከያ ሚኒስትር ፒስተርዮስ ከሚቀጥለው ዓመት ጀምሮ ከ3000 እስከ 5000 የሚደርሱ ተጨማሪ የፈቃደኝነት ምልመላዎች እንከናወኑ ይፈልጋሉ። እና 200, 000 መጠባበቂያ ኃይል እንዲኖር ይፈልጋል። አሁን ካለው 70 ሺህ ጋር በማነፃፀር መከላከያ ሚኒስቴር ጥያቄውን በጥልቀት እያየ ነው።በ18 ዓመት እድሜ ክልል ውስጥ ያሉ 300 ሺህ ገደማ ወጣት ወንዶች እዚህ በጀርመን ይገኛሉ።ስለዚህ በአሁኑ ወቅት እያሉ ያሉት በቂ እንዳልሆነ ከተረዱ መምረጥ ወይም አንዳንድ እንደ ሎተሪ ያሉ አማራጮችን ለመሞከር እንነጋገራለን ብለዋል። ቁጥሩ ትንሽ ከሆነ።»በማለት ገልፃለች።



ለወጣት ወንዶች አዳዲስ ግዴታዎች



ምንም እንኳን ወታደራዊ አገልግሎት በፈቃደኝነት የሚቆይ ቢሆንም፣ ሁሉም የ18 ዓመት ወንዶች ከ2026 ጀምሮ “የፈቃደኝነት መግለጫ” ተብለው መጠይቆችን መሙላት አለባቸው። ስለ አካላዊ ብቃታቸው እና በጦር ኃይሎች ውስጥ ለማገልገል ያላቸውን ፍላጎት በተመለከተ ለሚነሱ ጥያቄዎች መልስ መስጠት አለባቸው።ሁሉም የ18 አመት ታዳጊዎች፣ ከዳሰሳ ጥናቱ ጋር የሚያገናኝ የQR ኮድ ይቀበላሉ። ሴቶች ለመሙላት መምረጥ እና የጀርመን ጦር ውስጥ ለማገልገል ያላቸውን ፍላጎት መግለጽ ይችላሉ። ነገር ግን ይህ ግዴታ አይሆንም ምክንያቱም የጀርመን መሰረታዊ ህግ ወንዶች ብቻ ውትድርና መግባት እንዲችሉ ይደነግጋል።

በዚህ መሰረት ከጥር 2027 ጀምሮ ሁሉም የ18 አመት ወንዶች በ2008 ከተወለዱት ወንዶች ጀምሮ ለስራ ብቁ መሆናቸውን ለማረጋገጥ የህክምና ምርመራ ይደረግላቸዋል።ለእነዚህ የአካል ብቃት ምርመራዎች ኃላፊነት የሚወስዱት በመላ አገሪቱ የሚገኙ የውትድርና ጽሕፈት ቤቶች ናቸው። በጎርጎሪያኑ 2011 የግዴታ የውትድርና አገልግሎት እንዲያበቃ ሲደረግ እነዚህ ቢሮዎች ተዘግተው ነበር። የመከላከያ ሚኒስቴር አሁን አዲስ መሠረተ ልማት ለመገንባት እየተጣደፈ ነው። ለዚሁ ዓላማም የሚውሉ ንብረቶችንም እየፈተሸ ነው።



ትችት ከወጣቱ ትውልድ



የመንግስት በውትድርና አገልግሎት ላይ የወሰደው ስምምነት በተለይ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ወጣቶች ትችት እየገጠመው ነው። የተማሪዎች ተወካይ ኩንቲን ገርትነር ስምምነቱን በቂ አይደለም ሲሉ ተችተዋል። ዋና ፀሃፊው «ሬዳሲወንስኔትዌርክ ዶችላንድ » በጀርመንኛው ምህፃሩ (RND)ከሚባለው የጀርመን የዜና ድርጅት ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ የውትድርና አገልግሎት ህግ፤ በ100 ቢሊዮን ዩሮ የገንዘብ ድጋፍ በሚደረግለት “የወጣቶች የትምህርት እና የአእምሮ ጤና ዘመቻ”ን እንዲታጀብ ጠይቀዋል። ጋርትነር "መንግስት ለኛ ሀላፊነት ሊወስድ መዘጋጀቱን የሚያሳይ ትንሽ ምልክት እንኳን የለም" ብለዋል።



ፀሐይ ጫኔ

ታምራት ዲንሳ

Comments 
In Channel
loading
00:00
00:00
x

0.5x

0.8x

1.0x

1.25x

1.5x

2.0x

3.0x

Sleep Timer

Off

End of Episode

5 Minutes

10 Minutes

15 Minutes

30 Minutes

45 Minutes

60 Minutes

120 Minutes

ጀርመን ብሄራዊ ውትድርና አገልግሎት ምልመላ ልትጀምር ነው

ጀርመን ብሄራዊ ውትድርና አገልግሎት ምልመላ ልትጀምር ነው