ከታንዛኒያ ምርጫ ግጭት በኋላ ፖሊስ የወሰዳቸው ርምጃዎች እየወጡ ነው
Description
ስሙን መግለፅ ያልፈለገው ወጣት ታንዛኒያዊ የገጠመውን ነገር እስካሁን ማመን ተስኖታል። የ 32 ዓመቱ ወጣት በታንዛኒያ ከሁለት ሳምንት በፊት በተካሄደው ምርጫ ማግስት ነው ውኃ ሊያመጣ በወጣበት በፖሊስ ጥይት የተመታው።«ራሴን መሬት ላይ ነው ያገኘሁት። እግሬን ስመለከት ይደማል። ቀና ስል ፖሊስ ወደ እኔ አነጣጥሯል። እሄኔ ጭንቅላቴን ቢሆን ኖሮ ያገኙት አልቆልኝ ነበር።»
ዶይቸ ቬለ ለዚህ ዘገባ ጁማ ብሎ የሚጠራው ወጣት ስለገጠመው ነገር ሲናገር ይንቀጠቀጣል። «የዶይቸ ቬለ የቀረፃ ቡድን ምናልባት ሰላይ ይሆናል ብሎ ብዙ ካመነታ በኋላ ነው ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ስለ ደረሰበት ነገር እንዲያውቅ ለመናገር የፈቀደልን» ትላለች የዶይቸ ቬለ ዘጋቢ ኤዲት ኪማኒ
አወዛጋቢውን ምርጫ ተከትሎ በተፈጠረው ሁከት ምን ያህል ህይወት እንደጠፋ እስካሁን ይፋ አልሆነም ሆኖም በርካታ ምስሎች እና ቪዲዮዎች ኢንተርኔቱን እየሞሉ ነው። ከእነዚህ ተንቀሳቃሽ ምስሎች መካከል ከባድ መሣሪያ የታጠቁ ወንዶች አደባባይ ለተቃውሞ የወጡ ሰዎች ላይ ሲተኩሱ ይታያል።
እንደየተቃዋሚ ፓርቲ ቻዴማ እና የሰብአዊ መብት ተከራካሪ ድርጅቶች ከሆነ በብዙ መቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ተገድለዋል።
እኝህ የዳሬሰላም ነዋሪ የታዘቡትን ለዶይቸ ቬለ ገልፀዋል።«ከፍተኛ ዷ ዷ የሚል የተኩስ ድምጽ ሰማሁ። እዚህ ጋር፤ እዛ ጋር አስከሬን ነበር። ሌላ ደግሞ እዛ ጋር በደም የተጨማለቀ አስክሬን አየሁ። በጣም ግራ ስለገባኝ መሮጥ እንኳን አልቻልኩም። እውነት ነው ሰዎች ሞተዋል። ብዙ ሰዎች ሞተዋል። በአይኔ አይቻለሁ።«
ያልተረጋጋችው ታንዛንያ አካባቢውን የማተራመስ አቅም አላት
ዶይቸ ቬለ ይህንን ቀረጸ በቦታው ባደረገበት ወቅት፣ የቀረፃ ቡድኑ በታጠቁ ፖሊሶች በተደጋጋሚ ቁጥጥር ተደርጎበታል። ምርጫ ከተካሄደ ከሁለት ሳምንታት በኋላ በታንዛኒያ ትልቋ ከተማ ዳሬሰላም ህይወት በጥንቃቄ እና ቁጥጥር በተሞላበት ሁኔታ ቀጥሏል። ምክትል ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ንቺምቢያ ሁሉም ነገር ደህና ነው ይላሉ። «የፕሬዚዳንት ሳሚያ ሱሉሁ ሀሰን መንግስት በሀገሪቱ ያለውን አንድነት ለመመለስ እየሰራ ይገኛል። አሁን አገራችን ተረጋግታለች ። ሁሉም ሰው የህግ የበላይነትን እያከበሩ ነው።«
በዚህ ህግ መሠረት 400 የሚጠጉ ሰዎች ከምርጫ ጋር በተያያዙ ወንጀሎች ክስ ተመስርቶባቸዋል። ከእነዚህ መካከል በለጠፈችው ቪዲዮ ምክንያት በአገር ክህደት የተከሰሰችው ቲክቶከር ጄኒፈር ጆቪን ናት። ቪዲዮው ላይ ቲክቶከሯ ለተከታዮቿ ባስተላለፈችው መልዕክት በምርጫ ቀን ከአስለቃሽ ጭስ እንዲከላከልላቸው ጭምብል እንዲያጠልቁ ትመክራለች።
በእስረኞች ላይ እንግልት እየደረሰባቸው መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ። የተቃዋሚዎች ዋና ጠበቃ ፒተር ኪባታላ ይህ የማይካድ ሀቅ ነው ይላሉ።
« ሚስጥር አይደለም። ከባድ ስቃይ እንደደረሰባቸው ለፍርድ ቤት አስረድተናናል። አንዳንዶቹ እንደውም በግልፅ የሚታይ ውጫዊ የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል።»
አወዛጋቢውን ምርጫ በመቃወም በተነሳው ግጭት የተገደሉት ሰዎች ጉዳይ እንዲጣራ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ባለፈው ማክሰኞ ጥሪ አቅርቧል። ፖሊስ ከአስክሬን ማቆያ ስፍራ የነበረ አስክሬን ወደ ማይታወቅ ቦታ መውሰዱ ከተሰማ በኋላ የተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽነር ፎልከር ቱርክ “ማስረጃ ለመደበቅ እንደተሞከረ ግልጽ ነገር አለ” በማለት ባለስልጣናት የሟቾችን አስክሬን ለሟች ቤተሰቦች እንዲያስረክቡ እና ቀብራቸው እንዲፈፀም ጠይቀዋል።
ልደት አበበ
ታምራት ዲንሳ






















