DiscoverDW | Amharic - Newsሩሲያ በአፍሪካ የሕዝብ አስተያየት ለመለወጥ ምን እያደረገች ነው?
ሩሲያ በአፍሪካ የሕዝብ አስተያየት ለመለወጥ ምን እያደረገች ነው?

ሩሲያ በአፍሪካ የሕዝብ አስተያየት ለመለወጥ ምን እያደረገች ነው?

Update: 2025-01-30
Share

Description

የሩሲያ ዋና ከተማ ሞስኮን ያሳያል ተብሎ በፌስቡክ በተለጠፈ ፎቶግራፍ በብዛት ከተደረደሩ ቅንጡ ጀልባዎች ጀርባ ረዣዥም የመስታወት አንጸባራቂ ሕንጻዎች ይታያሉ። ፎቶው ትክክለኛ ቢሆንም አንድ ጉዳይ ግን ስህተት ነው። ፎቶው የተነሳው በሞስኮ ሳይሆን በዱባይ እንደሆነ የፎቶግራፎችን ትክክለኛነት ለማረጋገጥ በሚረዱ የድረ-ገጽ መፈለጊያዎች ማወቅ ይቻላል።



ፎቶግራፉን ያሰራጨው የፌስቡክ አካውንት በምሥራቅ አፍሪካዊቷ ብሩንዲ በሚገኝ ሰው የተከፈተ ለመሆኑ ስልክ ቁጥርን ጨምሮ በገጹ ላይ የሚገኙ መረጃዎች ይጠቁማሉ። ገጹ በሩሲያው ፕሬዝደንት ቭላድሚር ፑቲን ሥም የተከፈተ ነው። የፕሬዝደንቱ ፎቶግራፍ በዋና ምስልነት በሚገኝበት ገጽ አዘውትሮ ለሩሲያ መንግሥት አዎንታዊ ይዘት ያላቸው መልዕክቶች ይለጠፉበታል።



ከይዘቶቹ መካከል ውሸት የሆኑ ጭምር ይገኛሉ። ለምሳሌ ያክል የሩሲያ የጨረር የጦር መሣሪያ 750 የአሜሪካ ተዋጊ አውሮፕላኖች አወደመ የሚለው ውሸት ነው። ይህ ገጽ ከ180,000 በላይ ሰዎች ይከተሉታል። ፖለቲካዊ ተጽዕኖ ለማሳደር በገጹ የተለጠፉ ሁሉ ግን ውሸት አይደሉም።



አብዛኞቹ ትክክለኛነታቸውን ለመለየት የሚቸግር አይነት ናቸው። ሩሲያ ስልታዊ ጠቀሜታ ባላቸው የአፍሪካ ሀገራት ለራሷ አዎንታዊ ገጽታ ለመፍጠር እንደምትፈልግ የሚጠቁሙ መልዕክቶች አሉ።



የአሜሪካ ጦር ሠራዊት የጥናት እና ምርምር ክንፍ የሆነው የአፍሪካ ስትራቴጂካዊ ጥናት ማዕከል በመጋቢት 2024 ይፋ ባደረገው ሪፖርት ሩሲያ በአፍሪካ ተጽዕኖ ለመፍጠር ከፍ ያለ ጥረት እያደረገች እንደምትገኝ አትቷል። ገጽታ ለመገንባት ከሚደረጉ ወደ 200 የሚሆኑ ዘመቻዎች 80ዎቹ ከሩሲያ ተቋማት የሚመነጩ ናቸው። ይኸ ቻይና፣ የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች፣ ሳዑዲ አረቢያ እና ቃጣርን የመሳሰሉ ሀገራት ከሚያደርጉት የላቀ ነው። በአሜሪካ ጦር ሥር የሚገኘው ተቋም እንደሚለው ከሁለት ዓመታት በፊት ከተደረገ የዳሰሳ ጥናት ሲነጻጸር የሐሰተኛ መረጃ ሥርጭት በአራት እጥፍ መጨመሩን ሰንዷል።



እነዚህ ዘመቻዎች ሙሉ በሙሉ ሐሰተኛ በሆኑ ጉዳዮች ላይ እምብዛም መሠረት እንደማያደርጉ ልብ ማለት ያሻል። በምትኩ ትክክለኛ አላባቸው በግነት እና ሆን ተብሎ በሚደበቁ መረጃዎች የተዛቡ ናቸው። አንዳንድ ጊዜ ቀድሞም የነበረውን የሕዝብ አስተያየት በማጠናከር ለተፈለገው ዓላማ ማዋል ይቻላል።



የደቡብ አፍሪካው የዲጂታል አማካሪ ኩባንያ ሙርሙር ኢንተለጀንስ ተባባሪ መሥራች አልዱ ኮርኔሊሰን “በአፍሪካ ምሥራቅ እና ምዕራቡን የማነጻጸር ልማድ አለ። በዚህ ንጽጽር ብዙውን ጊዜ ምዕራቡ መጥፎ ወገን ነው። ይኸ ንጽጽር በአፍሪካ በሁሉም ውይይቶች ውስጥ በሚባል ደረጃ የሚገኝ ነው። ለዚህ ደግሞ ብዙ ሥራ አይጠይቅም፤ ማስታወስ ብቻ በቂ ነው። ለሰዎች ይህን ለማስታወስ መዋሸትም ሆነ ሐሰተኛ መረጃ ማሰራጨት አያስፈልግም” ሲሉ ተናግረዋል።



ኮርኔሊሰን በኩባንያቸው በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች የሚሰራጩ ይዘቶችን ለጥናት የሚፈልጓቸው መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች (think tanks) ጨምሮ ለደንበኞቻቸው ይተነትናሉ። ይኸ ሥራቸው በሩሲያ አማካኝነት ይካሔዳሉ የሚባሉ ዘመቻዎችን ይጨምራል።



አልዱ ኮርኔሊሰን “በአፍሪካ አውድ ቁልፍ ሚና ካላቸው አካውንቶች ጋር የተሳሰረ የዓለም አቀፍ ቁልፍ አካውንቶች ኔትወርክ አለ። በእያንዳንዱ ሀገር የወከሏቸው ተጽዕኖ ፈጣሪዎች አሏቸው። ይህ እየተሳሰረ ወደ ላይ እና ወደ ታች ያገናኛል” ሲሉ ተናግረዋል።



መቀመጫውን በሴኔጋል ዋና ከተማ ዳካር ያደረገው የስትራቴጂክ እና ዓለም አቀፍ ጥናት ማዕከል (CSIS) ባልደረባ ቤቨርሊ ኦቺየንግ ያረጋግጡት ነው። “ለምሳሌ ያክል በማሊ የሚገኝ አንድ የሲቪል ማኅበረሰብ ሲለው ከሩሲያ ባለሥልጣን የመጣ አይመስልም። የአካባቢውን ቋንቋ የሚናገር እና ከሕዝብ አቋም የሚቀራረብ ሰው ስሜት ነው የሚመስለው። ነገሩ የሚከወነው እንዲህ ባለ መንገድ ነው። እጅግ ውስብስብ ባይሆንም ድብቅ እና ስኬታማ ነው” ሲሉ ቤቨርሊ ኦቺየንግ አብራርተዋል።



ከዚህ ቀደም በሩቅ ይፈበረኩ የነበሩ የማኅበራዊ ድረ-ገጾች ሐሰተኛ መረጃዎች አሁን ቋንቋ እና የባሕል ልዩነቶችን ጠንቅቀው በሚያውቁ የሀገሬው ሰዎች የሚመረቱ ሆነዋል። ኮርኔሊሰን “ጥቃቅን ተጽዕኖ ፈጣሪዎች” ብለው ይጠሯቸዋል። በደቡብ አፍሪካ ያላቸውን እንቅስቃሴ የሰነዱት ተንታኝ እንደሚሉት ዝቅተኛም ቢሆን ሁሉም ይከፈላቸዋል። መረጃዎቹ ለብዙ ሰዎች እንዲደርሱ የሚያደርጉ አካውንቶችም አሉ። በሰው ወይም በማኅበራዊ ድረ-ገጾች በተፈጠሩ ቦቶች (bots) የሚዘወሩት አካውንቶች በመጋራት እና ሌሎች ተጠቃሚዎችን በስም በመጥቀስ ይዘቶቹ ከፍተኛ ዕይታ እንዲያገኙ ያደርጋሉ።



የትንተና እና የባህሪ ለውጥ ማዕከል (The centre for analytics and behavioural change) የተባለ ተቋም በደቡብ አፍሪካ የሚገኘው የሩሲያ ኤምባሲ ዙሪያ የሚገኙ የኤክስ ኔትወርኮችን እንቅስቃሴ ሰንዷል። የሩሲያ እና የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አፍቃሬ የሆነው ጃክሰን ሒንክል እና የተወሰኑ ራሳቸውን “አማራጭ ሚዲያ” (alternative Media) ብለው የሚጠሩ አክቲቪስቶች ሌሎች ቁልፍ አካውንቶች ናቸው



ሩሲያ ለዘመቻዋ የምትጠቀመው ስውር የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች አወቃቀሮችን ብቻ ሳይሆን በቀጥታ የራሷን ቻናሎች ጭምር ነው። ማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ ሩሲያ በአፍሪካ ያላት ተጽዕኖ መሞከሪያ ናት። ሌንጎ ሶንጎ የተባለው የራዲዮ ጣቢያ በ2018 በሩሲያ ሰላዮች እንደተመሠረተ ይነገራል።



ባለፈው ሕዳር በርካታ የአውሮፓ መገናኛ ብዙኃን ከሀገሪቱ የሸሸ ግለሰብ ሥራው እንዴት እንደሚከናወን ይፋ ያደረገውን ምስጢር የተመለከተ የምርመራ ዘገባ አቅርበዋል። ግለሰቡ ለጋዜጦች የሚጽፉ የሩሲያ ደጋፊ ባለሙያዎች መኖራቸውን አጋልጧል። የአንዳንዶቹ ይዘቶች ዝርዝር ጉዳዮች እንደ አገናኝ በሚያገለግሉ የሩሲያ ሰዎች የሚቀርቡ እንደሆኑ ገልጿል።



የሩሲያ መንግሥት የሚቆጣጠረው አርቲ (RT) የቴሌቭዥን ጣቢያም ስለ ሩሲያ አዎንታዊ ትርክት ለማሰራጨት ጥቅም ላይ ይውላል። ጀርመን እና የአውሮፓ ኅብረትን ጨምሮ በበርካታ የምዕራባውያን ሀገራት የቴሌቭዥን ጣቢያው ሥርጭት በከፊል ታግዷል።



በ2022 ቴሌቭዥን ጣቢያው በደቡብ አፍሪካ የእንግሊዘኛ ቋንቋ የሚሠራጭ ጣቢያ እንደሚያቋቁም ይፋ አድርጓል። ቦታው ሥራ መጀመሩን የአሜሪካ ድምጽ ዘግቧል። ሥርጭቱን “በበርካታ” የአፍሪካ ሀገራት በሳተላይት ማግኘት ይቻላል። በፈረንሳይኛ ተናጋሪ የአፍሪካ ሀገራት አርቲ (RT) የቴሌቭዥን ጣቢያ በፈረንሳይኛ ቋንቋ ይሰራጫል።



ሩሲያ በሳሕል ቀጠና የወሰደቻቸውን እርምጃዎች የሚያሞግሱ እና አልፎ አልፎም ከማሊ ወታደራዊ መንግሥት ግንኙነት ያላቸው የማሊ መገናኛ ብዙኃን ጋዜጠኞች እንደ ባለሙያ በተደጋጋሚ ይቀርባሉ። አፍሪካን ስትሪም (African Stream) የተባለውን የድረ-ገጽ መገናኛ ብዙኃን የሚቆጣጠረው አርቲ (RT) የቴሌቭዥን ጣቢያ እንደሆነ የቀድሞው ፕሬዝደንት ጆ ባይደን ሥልጣን ላይ ሳሉ የአሜሪካ ውጪ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ከሶ ነበር።



በአፍሪካ ላይ ያነጣጠሩ ሌሎች ቻናሎችም ተቋቁመዋል። መነሾው ከይቭጌኒ ፕሪጎዢን ኩባንያ ጋር የሚተሳሰረው “አፍሪካን ኢንሺየቲቭ” (African Initiative) በደንብ የሚታወቅ ነው። የቫግነር የግል ወታደራዊ ኩባንያ መሥራች የነበሩት ፕሪጎዢን በሰኔ 2023 ኃይላቸው ከፕሬዝደንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር ግብግብ ከፈጠረ ከጥቂት ሣምንታት በኋላ በአውሮፕላን አደጋ መሞታቸውን የሩሲያ ባለሥልጣናት አስታውቀዋል።



“አፍሪካን ኢንሼቲቭ” ራሱን የዜና አውታር አድርጎ የሚያቀርብ ሲሆን ሚናው በሩሲያ እና በአፍሪካ መካከል ‘ድልድይ’ መሆን እንደሆነ ይገልጻል። ሥራውን የሚያከናውነው በቴሌግራም እና በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ገጾች ሲሆን በከፊል በይፋ በከፊል ደግሞ በስውር ነው። በማሊ ከሚገኝ የጋዜጠኝነት ትምህርት ቤት ጋር ግንኙነት አበጅቷል። ባለፈው ታኅሳስ ሦስት የዓመቱ ምርጥ ተማሪዎች በቀጥታ በዘጋቢነት ተቀጥረዋል።



በቡርኪና ፋሶ ቢሮ ያለው ሲሆን ከጊዜ ወደ ጊዜ የተለያዩ መርሐ-ግብሮች እያዘጋጀ ነው። በግንቦት 2024 በኡጋዱጉ “አፍሪካን ኢንሼቲቭ” ባዘጋጀው መርሐ-ግብር ከ1945 “ሩሲያ በሒትለር ጀርመን ላይ የተቀዳጀችው ድል” እስከ “የአስር አመታት ጦርነት በዶንባስ“ የሚያሳዩ ፎቶዎች ለዕይታ አቅርቧል። ዶንባስ ሩሲያ ይገባኛል የምትለው የዩክሬን ግዛት ነው። የአካባቢው የመረጃ ምንጮች እንደሚሉት የቡርኪናቤ ሕዝብ “በሽብርተኞች ላይ ለተገኙ ወታደራዊ ድሎች የተሻለ አቀባበል አላቸው። ሩሲያ ያቀረበቻቸው መሣሪያዎች ወይም መሣሪያዎቹን የታጠቁ ወታደሮች በቀላሉ የትብብሩ ስኬታማነት ማረጋገጫ ተደርገው ይታያሉ።”



የሩሲያ ወታደራዊ ጥንካሬ በመዝናኛው ኢንዱስትሪ የሚቀርብ ይዘት ነው። በ2021 የተሠራው “ቱሪስት” የተሰኘ ፊልም ጀግና ገጸ-ባህሪ ለምሳሌ በማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ የሚገኝ የሩሲያ ወታደር ነው። “አፍሪካን ኢንሼቲቭ” ያቀረበው “አፍሪካ ዶውን” የተባለ የቪዲዮ ጨዋታ ተጫዋቾች ከሳሕል ወታደሮች እና ከሩሲያ ረዳቶቻቸው ወይም በፈረንሳይ እና በአሜሪካ ከሚደገፈው የምዕራብ አፍሪካ ማኅበረሰብ (ኤኮዋስ) አባል ሀገራት የፈለጉትን መምረጥ ይችላሉ።



እንዲህ አይነቱ ወታደራዊ ጉዳዮችን ከመዝናኛ የማዋሃድ አካሔድ አነሰም በዛ በዘዴ የሚተላለፈውን ዋና መልዕክት ለመደገፍ የታለመ ነው። ይኸም የቅኝ ገዢዎች ዘመን አብቅቷል፤ የተሻለችው አጋር ሩሲያ ዝግጁ ነች የሚል ነው። ለእንዲህ አይነቶቹ መልዕክቶች መደበኛ አጋጣሚዎች አሉ። የፈረንሳይ ፕሬዝደንት ኤማኑዌል ማክሮ በጥር 6 የአፍሪካ መንግሥታት “አናመሰግናለን ማለት” ረስተዋል ሲሉ ቁጣው ኃይለኛ ነበር።



“አፍሪካን ኢንሼቲቭ” የተሰጡ አስተያየቶችን በማሰባሰብ የአፍሪካ ሀገሮችን በበለጠ ክብር የሚያስተናግዱ እንደ ሩሲያ ያሉ ‘አማራጭ ተጫዋቾች ሊፈጠሩ ያስፈልጋል’ የሚል ድምዳሜ ላይ ከደረሱት የሴንት ፒተርስበርግ የፖለቲካ ሳይንቲስት አስተያየት ጋር አያያዘው። በ20ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ለዚህ ማመሳከሪያ የሚሆኑ ጉዳዮች አሉ። የቀድሞዋ ሶቭየት ኅብረት የደቡብ አፍሪካው የአፍሪካ ብሔራዊ ኮንግረስ (ANC) እና የህዝቦች ንቅናቄ ለአንጎላ ነጻነት የመሳሰሉ የትጥቅ ትግሎችን ደግፋለች። በኢትዮጵያ፣ በሶማሊያ እና በዛሬዋ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ የቀድሞ አዳዲስ መንግሥታትንም ታግዝ ነበር።



“ሩሲያ አዳዲስ መንግሥታትን እንደምትደግፍ መካድ አይቻልም – ይህ ያለ ነው። ከመጀመሪያው አንስቶ ከእኛ ጋር ስለጀመሩ ሩሲያ ለዓመታት ወዳጅ ሆና ቆይታለች። ነገር ግን በተወሰነ መንገድ የተጋነኑ ናቸው። ከዚህ በተጨማሪ በፈረንሳይ እና በምዕራቡ ላይ በተቀሰቀሰ ቁጣ ላይ የተደረበ ነው” ሲሉ የስትራቴጂክ እና ዓለም አቀፍ ጥናት ማዕከል (CSIS) ባልደረባ ቤቨርሊ ኦቺየንግ ተናግረዋል።



በበርካታ የአፍሪካ ሀገራት ይህ መልሶ እያቆጠቆጠ ይመስላል።



ዴቪድ ኢል/እሸቴ በቀለ

Comments 
In Channel
loading
00:00
00:00
x

0.5x

0.8x

1.0x

1.25x

1.5x

2.0x

3.0x

Sleep Timer

Off

End of Episode

5 Minutes

10 Minutes

15 Minutes

30 Minutes

45 Minutes

60 Minutes

120 Minutes

ሩሲያ በአፍሪካ የሕዝብ አስተያየት ለመለወጥ ምን እያደረገች ነው?

ሩሲያ በአፍሪካ የሕዝብ አስተያየት ለመለወጥ ምን እያደረገች ነው?