DiscoverDW | Amharic - Newsየኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር የገጠሙት ተግዳሮቶች “አብዛኞቹ ፖለቲካዊ” መሆናቸው ተገለጸ
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር የገጠሙት ተግዳሮቶች “አብዛኞቹ ፖለቲካዊ” መሆናቸው ተገለጸ

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር የገጠሙት ተግዳሮቶች “አብዛኞቹ ፖለቲካዊ” መሆናቸው ተገለጸ

Update: 2025-11-17
Share

Description

ከተጀመረ ሦስት ዓመታት ከመንፈቅ ገደማ ያስቆጠረው የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ሒደት “የመጨረሻ ምዕራፍ” ላይ መድረሱን ሒደቱን የሚመሩ ኮሚሽነሮች ገልጸዋል። በሒደቱ ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ ለመጥራት “ጫፍ” ላይ ቢደረስም መፍትሔ የሚፈልጉ በርካታ ችግሮች መኖራቸውን የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ዋና ኮሚሽነር መስፍን አርዓያ ባለፈው ዓርብ ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በተደረገ ውይይት ላይ ተናግረዋል።



“ሀገራዊ የምክክሩ ሒደት እስካሁን በደረሰበት ምዕራፍ” ያጋጠሙትን ችግሮች የዘረዘሩት ዋና ኮሚሽነሩ “አብዛኞቹ ፖለቲካዊ በመሆናቸው ፖለቲካዊ መፍትሔ ያስፈልጋቸዋል ብለን እናምናለን” ሲሉ ተደምጠዋል።



“የትግራይ ሕዝብ ውክልና” አለማግኘት የኮሚሽኑን ኃላፊዎች “ከጊዜ ጋር ሩጫ ውስጥ” እንዲገቡ ካደረጓቸው ጉዳዮች አንዱ መሆኑን ኮሚሽነር መላኩ ወልደማርያም ተናግረዋል። “የትግራይ ሕዝብ በምክክሩ ሒደት እንዲካተት እና ትርጉም ያለው ተሳትፎ እንዲኖረው” የኢትዮጵያ ፌዴራል መንግሥት እና ህወሓት ግጭት የማቆም ሥምምነት ከተፈራረሙ በኋላ ኮሚሽኑ የተለያዩ ጥረቶች ሲያደርግ መቆየቱን ኮሚሽነር መላኩ ገልጸዋል።



“በክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር እና የተለያዩ ባለድርሻ አካላት በኩል አብዛኛው ፖለቲካዊ ይዘት ያላቸው እና ከፕሪቶሪያ ሥምምነት አተገባበር ጋር የተያያዙ ጥያቄዎች” መቅረባቸውን የገለጹት ኮሚሽነር መላኩ “በአብዛኛው ከፌዴራል መንግሥት ጋር የተያያዙ” በመሆናቸው “ለመንግሥት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች በማቅረብ መፍትሔ እንዲፈለግላቸው በእኛም በኩል ግፊት ስናደርግ ቆይተናል” ሲሉ አብራርተዋል።



ይሁንና “ችግሮቹ ባለመፈታታቸው የጀመርንው ሥራ በዕቅዳችን መሠረት መከናወን አልቻለም” ሲሉ ሒደቱ የሚገኝበትን አስረድተዋል። በዚህም ሳቢያ በሌሎች የኢትዮጵያ ክልሎች የተከናወነው “የተሳታፊ ልየታ እና የአጀንዳ ማሰባሰብ ሥራ” በትግራይ አልተከናወነም።



የኮሚሽኑ ኃላፊዎች ከኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች 80 በመቶ ያህሉ “በምክክር ሒደቱ ተካትተው ንቁ ተሳትፎ እያደረጉ” መሆናቸውን ገልጸዋል። ይሁንና የፓርቲዎቹ ተሳትፎ “ምሉዕ አለመሆን” የኢትዮጵያን ችግሮች ለመፍታት ላቀደው ምክክር ፈተና ነው።



የተቃዋሚ ፓርቲዎች ኮከስ አባላት “ከጅምሩ ያልተሳተፉ” መሆናቸውን ኮሚሽነር መላኩ ተናግረዋል። የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) ፣ የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ) እና እናት ፓርቲዎች በአማራ ክልል ከተካሔደው የአጀንዳ ማሰባሰብ መድረክ ጀምሮ “ተሳትፎ ያቋረጡ” ናቸው።



የኦሮሞ ነጻነት ግንባር፣ የኦሮሞ ፌደራላዊ ኮንግረስ፣ መኢአድ፣ ኢሕአፓ እና የእናት ፓርቲ አመራሮችን ወደ ኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ጽህፈት ቤት በመጥራት “በሚያነሷቸው ጉዳዮች ዙሪያ” ንግግር መደረጉን ኮሚሽነር መላኩ ጠቅሰዋል። “አብዛኛዎቹ የሚያነሷቸው ጉዳዮች ከሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ጋር የተያያዘ አይደለም። አብዛኛዎቹ የሚያነሷቸው ጉዳዮች ከመንግሥት ጋር የተያያዙ ጉዳዮች ናቸው” ሲሉ አስረድተዋል።



የፖለቲካ ፓርቲዎቹን ሥጋቶች በተመለከተ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን “አስፈላጊውን ነገር ለማድረግ” መሞከሩን የገለጹት ኮሚሽነሩ ይሁንና ተቋሙ “ውሳኔ ሰጪ አካል” ባለመሆኑ መፍትሔ ሊያበጅላቸው እንደማይችል ጠቁመዋል።



በሒደቱ የማይሳተፉ የፖለቲካ ፓርቲዎች በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች በመካሔድ ላይ የሚገኙ “ግጭቶች መቆም አለባቸው”፤ “በፖለቲካ አመለካከታቸው ምክንያት የታሠሩ የፖለቲካ እስረኞች መለቀቅ አለባቸው” የሚል አቋም እንዳላቸው ኮሚሽነር መላኩ ተናግረዋል። ከሀገራዊው ምክክር በፊት “በመንግሥት እና በፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል ፖለቲካዊ ድርድር መደረግ አለበት” የሚል ሐሳብ ለኮሚሽኑ ቀርቦለታል።



ፋኖ እና የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊትን ጨምሮ ከመንግሥት ጋር የሚዋጉ ታጣቂ ኃይሎች “ሀገራዊ መግባባት” ለማምጣት በታቀደበት የምክክር ሒደት እንዲሳተፉ ከዚህ ቀደም ተደጋጋሚ ጥሪዎች ሲቀርቡ ቆይተዋል። “የታጣቂ ኃይሎች ተወካይ ነን” ወይም “ግንኙነት አለን” ከሚሉ ወገኖች ጋር በኢትዮጵያ ውስጥ እና በውጪ ሀገራትም ውይይቶች ተደርገዋል።



ታጣቂ ኃይሎችን የተመለከቱ ውይይቶች የተደረጉት ከፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ከኃይማኖት ተቋማት፣ ከምርጫ ቦርድ፣ ከሚዲያዎች፣ ከፌድራል እና የክልል የሥራ ኃላፊዎች፣ ከሲቪክ ማኅበራት ፣ ከተለያዩ ሀገራት ኤምባሲዎች፣ ዓለም አቀፍ ቀይ መስቀልን የመሳሰሉት ተቋማት ጋር ጭምር ነው። ኮሚሽነር መላኩ “መፍትሔ የሚፈለግበትን፤ መፍትሔ የሚበጅበትን ሁኔታ ለማመቻቸት ኮሚሽኑ የሚችለውን አድርጓል” ሲሉ ተደምጠዋል።



የኮሚሽኑ ኃላፊዎች ከተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የተውጣጡ ተሳታፊዎች በተለዩ አጀንዳዎች ላይ የሚወያዩበትን ሀገራዊ ጉባኤ በተያዘው ዓመት የማካሔድ ዕቅድ አላቸው። ሀገራዊው ምክክር እና ሰባተኛው አጠቃላይ ምርጫ የሚካሔዱበት ጊዜ መደራረብ “ራሱን የቻለ ተግዳሮት” ሆኗል።



የዎላይታ ብሔራዊ ንቅናቄ እና አረና ትግራይ ለዴሞክራሲና ለሉዓላዊነትን ጨምሮ ዐሥር ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ግን ከምርጫው በፊት “ብሔራዊ መግባባት መገንባት እና በውጭ ሀገራት እና በትጥቅ ትግል ላይ የሚገኙትን ጨምሮ ከሁሉም የፖለቲካ ኃይሎች እና ባለድርሻዎች ጋር በሚደረግ ሁሉን አካታች ውይይት እርቅ ማውረድ ያስፈልጋል” የሚል አቋም አላቸው።



ፓርቲዎቹ “በሀገሪቱ አንገብጋቢ ጉዳዮች ላይ ሰፊ ውይይት እና ድርድር” ተደርጎ ሥምምነት ላይ ሳይደረስ “የሚካሔድ ምርጫ የፖለቲካ ቀውሱን ከማባባስ ባለፈ መፍትሔ ሊያመጣ አይችልም” ሲሉ አስጠንቅቀዋል።



ኦነግ፣ ኦፌኮ እና ኅብር ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ድርጅትን ጨምሮ 10 የፖለቲካ ፓርቲዎች ከሁለት ሣምንት በፊት በጋራ ያወጡት መግለጫ በመካሔድ ላይ በሚገኘው ሀገራዊ ምክክር እምነት እንደሌላቸው የሚጠቁም ነው። ፓርቲዎቹ “ለእውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ሽግግር የጋራ የሆነ ፍኖተ-ካርታ” ለማዘጋጀት “መንግሥት በአፋጣኝ ሁሉን አቀፍ የፖለቲካ ውይይት” እንዲጀምር ጥሪ አቅርበው ነበር።



ገዥው ብልጽግና ፓርቲ እና መንግሥት ግን ሰባተኛው አጠቃላይ ሀገራዊ ምርጫ በታቀደለት ጊዜ ይካሔዳል የሚል አቋም አላቸው። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ሀገራዊ ምክክሩ ግንቦት 24 ቀን፣ 2018 ዓ.ም ሊካሔድ ጊዜያዊ ቀጠሮ ከተያዘለት ምርጫ ጋር “ምንም ትሥሥር” የለውም የሚል አቋም እንዳላቸው ለተወካዮች ምክር ቤት ተናግረዋል። “ምርጫን የሚያስቆም ምክክር አንፈልግም” ያሉት ዐቢይ “ምርጫ ጊዜውን ጠብቆ የሚፈጸም ይሆናል” ሲሉ አስረድተዋል።



አርታዒ ማንተጋፍቶት ስለሺ

Comments 
In Channel
loading
00:00
00:00
x

0.5x

0.8x

1.0x

1.25x

1.5x

2.0x

3.0x

Sleep Timer

Off

End of Episode

5 Minutes

10 Minutes

15 Minutes

30 Minutes

45 Minutes

60 Minutes

120 Minutes

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር የገጠሙት ተግዳሮቶች “አብዛኞቹ ፖለቲካዊ” መሆናቸው ተገለጸ

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር የገጠሙት ተግዳሮቶች “አብዛኞቹ ፖለቲካዊ” መሆናቸው ተገለጸ

Eshete Bekele