በደቡብ አፍሪቃ ቢያንስ አምስት ኢትዮጵያዊያን በአንድ ሳምንት ጊዜ ዉስጥ ተገደሉ
Description
ደቡብ አፍሪቃ ውስጥ ኢትዮጵያውያን በታጣቂዎች ሲገደሉ የባለፈው ሳምንቱ የመጀመሪያ አይደለም። በሀገሪቱ መጤ ጠሎች፣ ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ ጥቁር አፍሪቃውያንን ሲገድሉና ሲዘርፉ ብዙ ዓመታት ተቆጥረዋል። ከዚሁ ጋር ወንጀለኞችም አድብተው ኢትዮጵያውያንን እንደሚገድሉ ይሰማል። የተባበሩት የኢትዮጵያውያን ማኅበረሰብ ማኅበር እና አንድ የማኅበረሰብ እንቂ ለዶቼቬለ እንደተናገሩት ባለፈው ሳምንት በጆሀንስበርግና አካባቢው እንዲሁም በደርባን ከተማ ነፍሰ ገዳዮች ኢትዮጵያውያኑ ቤት ወይም የንግድ ድርጅት ሄደው እንዲሁም በጠራራ ፀሐይ በመንገድ ላይ ነው ኢትዮጵያውያኑን የገደሉት።
አቶ ዮሐንስ ሃቢብ መቀመጫውንበደቡብ አፍሪቃየንግድ ከተማ ጆሀንስበርግ ያደረገው በደቡብ አፍሪቃ የተባበሩት የኢትዮጵያውያን ማኅበረሰብ ማኅበር ወይም በእንግሊዘኛ መጠሪያው (United Ethiopian communities Association in South Africa) የተባለው ማኅበር ፕሬዝዳንት ናቸው። ባለፈው ሳምንት ከተገደሉት ኢትዮጵያውያን መካከል በጆሀንስበርግ ከተማ በመኪና ይጓዙ የነበሩ አንድ ኢትዮጵያዊ እንደሚገኙበት አቶ ዮሐንስ ለዶቼቬለ ተናግረዋል። ሌሎች ሁለት ኢትዮጵያውያንም በተመሳሳይ ወንጀለኞች በደርባን ከተማ ተገድለዋል ብለዋል። አቶ ዮሐንስ እንደተናገሩት ከመካከላቸው አንዱ በጣም አሰቃቂ በሚባል መንገድ ነውየተገደሉት።
ዶቼቬለ ያነጋገራቸው በደርባንየደቡብ አፍሪቃ የፍትህ ቢሮ ሠራተኛ እና የማኅበረሰብ አንቂ አቶ ኮስሞስ ገብረ ሚካኤል በሚኖሩባት በሌላኛዋ የደቡብ አፍሪቃ ከተማ በደርባን በዚሁ ባለፈው ሳምንት የተገደሉት ኢትዮጵያውያን ቁጥር ከሦስት በላይ ነው ብለዋል። ከመካከላቸው እርሳቸው በቅርብ የሚያውቋቸው ሰው ይገኙበታል። በጆሀንስበርግ ስለተገደሉትም መረጃ አላቸው።
አቶ ኮስሞስም ሆነ አቶ ዮሐንስ እንደሚናገሩት በአሁኑ ጊዜ በደቡብ አፍሪቃበውጭ ዜጎች ላይ የሚፈጸመው ጥቃት በተለይ በጥቁር ደቡብ አፍሪቃውያንላይ ያነጣጠረ ነው። የዚህም ምክንያቱ እንደ አቶ ኮስሞስ በሀገሪቱ ስለጥቁር አፍሪቃውያን የሚነገረው የጥላቻ ትርክት እየተበራከተ መሄዱ ነው። ይህም የግድያው መጠን በዚያው ልክ እየጨመረ እንዲሄድ አድርጓል ይላሉ አቶ ኮስሞስ ።
አቶ ዮሐንስ በበኩላቸው በተለይ የባለፈው ሳምንቱ ዓይነት ታጣቂዎች አድብተው በጥቁር አፍሪቃውያን ላይ ግድያዎች ሊፈጸሙ የሚችሉባቸው የሚባሉ ምክንያቶችም አሉ። ስለባለፈው ሳምንቱ በደቡብ አፍሪቃ በኢትዮጵያውያን ላይ ስለደረሰው ግድያበደቡብ አፍሪቃ የኢትዮጵያ አምባሳደርን አስተያየት ለማካተት ብንደውልም ለዛሬ አልተሳካም።
ኂሩት መለሰ
ማንተጋፍቶት ስለሺ























