በአማራ ክልል ወደ 4 ሚሊዮን ታዳጊዎች ት/ቤት አይሄዱም ተባለ
Description
በአማራ ክልል እድሜያቸዉ ለትምህርት ከደረሱ እና ይመዘገባሉ ተብሎ ታቅዶ ከነበረዉ 7 ሚልየን ተማሪዎች ዉስጥ 2.3 ሚልየን ተማሪዎች ናቸዉ 2017 ዓ.ም ወደ ትምህርት ገበታቸዉ የመጡት ለአብነትም በክልሉ በደቡብ ጎንደር ዞን የላይ ጋይንት ወረዳ በዘንድሮ የትምህርት ዘመን 142 የትምህርት ተቋማት የመማር ማስተማር ተግባሩን ይቀጥላሉ ተብሎ ቢታሰብም በማስተማር ላይ ያሉት ግን 17 ትምህርት ቤቶች ብቻ ናቸዉ ይላሉ የወረዳዉ ትምህርት ፅህፈት ቤት ተወካይ ኃላፊ አቶ ጌታቸዉ አዘዘ።
በክልሉ ያለዉ የፀጥታ ችግር በትምህርት ዘርፉ ላይ ያሳደረዉ ተፅኖ የጎላ እንደሆነ የሚናገሩት የሰሜን ወሎ ዞን ትምህርት መምሪያ ኃላፊ አቶ ፍትህ ታደሰ የመማር ማስተማሩ የተቋረጠባቸዉን አካባቢዎች ዳግም ወደ ትምህርት ለማስገባት እየተሰራ ነዉ ነገር ግን በዞኑ የማንነት ጥያቄ ያለባቸዉ አካባቢዎች አሁንም ከመማር ማስተማር ዉጭ ናቸዉ ይላሉ
< ብግና ላስታ ቆላማዉ አካባቢዎች መቄት ከወሰድን ጉባላፍቶም በመስመር ላይ ያሉትን የመማር ማስተማር እንዲቀጥሉ ምክክር እየተደረገ እየተሰራ ነዉ ያለዉ 100 ፐርሰንት ትምህርት ቤት ከፍተዉ እያስተማሩ ያሉ 7 ወረዳዎች አሉ በከፊል የሚያስተምሩ ወደ አራት ወረዳዎች ሲሆኑ ሙሉ በሙሉ የመማር ማስተማር የተቋረጠባቸዉ የማንነት ጥያቄ ያለባቸዉ ሦስት ወረዳዎችና ዳዉንት ወረዳ በአሁኑ ሰአት ሙሉበሙሉ መማር ማስተማሩ የተቋረጠባቸዉ ናቸዉ>
400ሺህ ተማሪዎች ትምህርት ማቋረጥ
የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮም በትምህርት አመቱ ከመዘገባቸዉ 2.7 ሚልየን ተማሪዎች መካከልም ከስድስት ወራት በኃላም 400 ሺህ የሚጠጉ ተማሪዎች በትምህርት ገበታቸዉ ላይ አለመሆናቸዉን ወይዘሮ እየሩስ መንግስቱ የትምህርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ ይናገራሉ
በሀገር አቀፍ ፈተና የክልሉ ተማሪዎች ዉጤት ዝቅ ማለት
የአማራ ክልል በግጭት ዉስጥ በቆየባቸዉ ግዚያት የክልሉ ተማሪዎች አጠቃላይ ዉጤት ዝቅ ማለቱን ተከትሎ ዘንድሮ ለ12ተኛ ክፍል ብሄራዊ ፈተና ላይ የተሻለ ዉጤት እንዲገኝ እየተሰራ መሆኑን የክልሉ ትምህርት ቢሮ ይገልፃል
ሦስተኛ ዙር የተማሪዎች ምዝገባ
አሁንም በክልሉ ወደ ትምህርት ቤት ይመጣሉ ተብለዉ ታስበዉ የነበሩ ተማሪዎችን ወደ ትምህርት ገበታቸዉ ለመመለስ እስከ ቀጣዮ የካቲት 30 ድረስ የሦስተኛ ዙር የተማሪዎች ምዝገባ ይካሄዳል ሲሉ የክልሉ ትምህርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ ይናገራሉ።
ኢሳያስ ገላዉ
አዜብ ታደሰ
ፀሐይ ጫኔ























