DiscoverDW | Amharic - Newsየማርበርግ ተሐዋሲ ምንነትና ሊደረግ የሚገባው ጥንቃቄ
የማርበርግ ተሐዋሲ ምንነትና ሊደረግ የሚገባው ጥንቃቄ

የማርበርግ ተሐዋሲ ምንነትና ሊደረግ የሚገባው ጥንቃቄ

Update: 2025-11-18
Share

Description

የተሐዋሲው አነሳስ



ማርበርግ ተሐዋሲ በይፋዊ አጠራሩ ማርበርግ ሄሞሮጂክ ፊቨር የሚባለው ሰዎችን ለሞት የሚያደርስ በሽታ መሆኑን የዓለም የጤና ድርጅት ያመለክታል። እንደ ድርጅቱ መረጃ ከሆነ በዚህ ተሐዋሲ ከተያዙ ሰዎች መካከል 50 በመቶው ሕይወታቸውን ያጣሉ። ተሐዋሲው ለመጀመሪያ ጊዜ የታወቀው በጎርጎሪዮሳዊው 1967 ዓም በጀርመኗ ማርበርግ እና ፍራንክፈርት ከተሞች፤ እንዲሁም ቤልግሬድ ሰርቢያ ውስጥ በተከታታይ መከሰቱን ተከትሎ ነው። የተዋሐሲው ወረርሽኝ ለመከሰቱ ምክንያት የሆነው ደግሞ ከዩጋንዳ በመጡ የጦጣ ዝርያዎች ላይ የተካሄደ ምርምር መሆኑን የዓለም የጤና ድርጅት ገልጧል። ከዚያ በመቀጠል ተሐዋሲው በወረርሽኝ መልክ እና ካለፍ አገደም በአንጎላ፤ በዴሞክራቲክ ኮንጎ፤ በኢኳቶሪያል ጊኒ፤ በጋና፤ በጊኒ፤ በኬንያ፤ እንዲሁም ከዚምባቡዌ በተጓዘ ግለሰብ አማካኝነት በደቡብ አፍሪቃ፤ ታንዛኒያ እና ዩጋንዳ ውስጥም መከሰቱን የድርጅቱ መረጃ ያመለክታል። በጎርጎሪዮሳዊው 2024 ዓም ደግሞ ሩዋንዳ፤ በያዝነው ጎርጎሪዮሳዊ ዓመት መጀመሪያ ላይ ደግሞ ታንዛኒያ ውስጥ ተከስቶ እንደነበርም ዐሳውቋል።



የማርበርግ ተሐዋሲ ምንነት



ማርበርግ ተሐዋሲ ለሕልፈተ ሕይወት በመዳረግ ከሚታወቁ ኃይለኛ ከሚባሉ የኤቦላ ተሐዋሲ ቤተሰብ ከሆኑት አንዱ መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ። ይህ ተሐዋሲ ሰሞኑን በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጂንካ ዞን መከሰቱ ተሰምቷል። ተሐዋሲው የሰው ሕይወትንም ቀጥፏል። የውስጥ ደዌ እና ተላላፊ በሽታዎች ተባባሪ ፕሮፌሰር የሆኑት ዶክተር ወንድወሰን አሞኘ ከኤቦላ ጋር ስለሚመሳሰለው ማርበርግ ተሐዋሲ ምንነት ሲገልጹ ማርበርግ ተሐዋሲ ከሌሊት ወፍ ከሚወጣ ፈሳሽ ጋር በሚኖር ንክኪ የሚመጣ አደገኛ ተሐዋሲ እንደሆነ ነው ባለሙያው የተናገሩት።



የበሽታው ምልክት



የማርበርግ ተሐዋሲ እንደ ኤቦላ ሁሉ የትኩሳት፤ ሳል፤ ማስመለስ እና ማስቀመጥ፤ እንዲሁም ከሰውነት ደም መፍሰስ የበሽታው ዓይነተኛ ምልክቶች መሆናቸው ይነገራል። ዶቼ ቬለ ካነጋገራቸው የጂንካ ከተማ ነዋሪዎች አንዱ እንደገለጹት ባለፈው ሳምንት በአካባቢያቸው ድንገት ታምመው ወደ ሀኪም ቤት ከሄዱ በኋላ ሕይወታቸው ያለፈው ወገኖች ተመሳሳይ የህመም ምልክት ታይቶባቸዋል።



የውስጥ ደዌ እና ተላላፊ በሽታዎች ተባባሪ ፕሮፌሰር ዶክተር ወንድወሰን ከኤቦላ ጋር የሚመሳሰለው የማርበርግ ተሐዋሲ የበሽታ ምልክቶችም ተመሳሳይ መሆናቸውን በመግለጽ ምልክቶቹ እንደ ትኩሳት፤ ማስቀመጥና ማስመለስ እንዲሁም የደም መፍሰስን እንደሚያካትቱ አስረድተዋል።





መተላለፊያ መንገድ



ኤቦላም ሆነ ማርበርግ ተሐዋሲ በበሽታው ከተያዘ ሰው በሚወጣ በማንኛውም ፈሳሽ አማካኝነት እንደሚተላለፍ ነው የተገለጸው። የውስጥ ደዌ እና ተላላፊ በሽታዎች ረዳት ፕሮፌሰር ዶክተር ወንድወሰንም እንደገለጹልን በሌሊት ወፍ ንክኪ አማካኝነት የሚመጣው ማርበርግ ተሐዋሲ በትንፋሽ ሳይሆን በተመሳሳይ መንገድ በመነካካት እንደሚተላለፍ ያስረዳሉ። እንዲህ ቢባልም ግን ሩዋንዳ ውስጥ እንደታየው ተገቢውን ጥንቃቄ ማድረግ ከተቻለ በሰዎች ሕይወት ላይ ሊያደርስ የሚችለውን ጉዳት መቀነስ ይቻላልም ባይ ናቸው።



ማርበርግ ተሐዋሲው ባለሙያው እንደገለጹት የሚተላለፍበት መንገድ ግልጽ ነው፤ በትንፋሽ ሳይሆን በአካል በቅርበት ንክኪ ሲኖር ነው። ባለፈው ሳምንት ዶቼ ቬለ ያነጋገራቸው የጂንካ ከተማ ነዋሪ የበሽታው ምንነት ሳይረጋገጥ ታምመው ወደ ጂንካ ሆስፒታል ተወስደው ሕይወታቸው ያለፈውወገኖች ቤተሰቦች እሳቸው እንደሚሉት ወዲያው ስላልታመሙ ኅብረተሰቡ በሽታው ተላላፊ ነው የሚለውን ለመቀበል ግራ ተጋብቶ ነበር። ጥርጣሬያቸውም ሟቾቹ ተመርዘው ይሆናል የሚል በመሆኑ ከታማሚዎቹ ጋር የቅርበት ንክኪ የነበራቸው ወገኖች አልታመሙምም ነው ያሉን።



ሊደረግ የሚገባው ጥንቃቄ



ይህ ማለት ግን ሰዎቹ በተሐዋሲው መያዝ አለመያዛቸው አልታወቀም ሊሆን ይችላል። ማርበርግ ተሐዋሲ ወደ ሰዎች ሲተላለፍ የበሽታው ምልክት እስኪታይ ቀናት ሊወስድ እንደሚችል የዓለም የጤና ድርጅት መረጃ ያስረዳል። ተሐዋሲው በተከሰተባቸው አካባቢዎች እንዲህ ያሉ መዘናጋቶች እንዳይኖሩ ዶክተር ወንድወሰን ሊደረግ የሚገባውን አስረድተዋል።



እንዲህ ያሉ ተላላፊ በሽታዎች የመተላለፊያ መንገዱን በመረዳት ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግንይጠይቃሉ። ያን ለማድረግ ደግሞ ማኅበረሰቡ ተሐዋሲው የሚተላለፍበትን መንገድ በአግባቡ እንዲረዳው ደጋግሞ ማስረዳት ግድ መንገር ያስፈልጋልና የውስጥ ደዌና ተላላፊ በሽታዎች ተባባሪ ፕሮፌሰሩ ዶክተር ወንድወሰንም ኅብረተሰቡ እንዲጠነቀቅ መልእክት አስተላልፈዋል።



እስካሁን በማርቡርግ ተሐዋሲ መያዛቸው የተረጋገጠ ሦስት ሰዎች መሞታቸውን የጤና ሚኒስቴር ዐሳውቋል። ሌሎች ሦስት ሰዎችም በተመሳሳይ የኅመም ምልክት መሞታቸውንም እንዲሁ። ከታመሙ ሰዎች ጋር ንክኪ የነበራቸው ከ10 በላይ ሰዎችም እራሳቸውን አግልለው ክትትል እየተደረገላቸው እንደሆነ ተገልጿል። መሠረታዊው ነገር ሰዎች ማርቡርግ ተሐዋሲ የሚያስከትላቸውን ምልክቶች ማወቅ፤ በትንፋሽ እንደማይተላለፍ መረዳትና፤ ከታመሙ ሰዎች ጋር የሚደረጉ ንክኪዎች ላይ ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ ነው። ለሰጡን ማብራሪያ የውስጥ ደዌና ተላላፊ በሽታዎች ተባባሪ ፕሮፌሰሩን እናመሰግናለን።



ሸዋዬ ለገሠ



ማንተጋፍቶት ስለሺ

Comments 
In Channel
loading
00:00
00:00
x

0.5x

0.8x

1.0x

1.25x

1.5x

2.0x

3.0x

Sleep Timer

Off

End of Episode

5 Minutes

10 Minutes

15 Minutes

30 Minutes

45 Minutes

60 Minutes

120 Minutes

የማርበርግ ተሐዋሲ ምንነትና ሊደረግ የሚገባው ጥንቃቄ

የማርበርግ ተሐዋሲ ምንነትና ሊደረግ የሚገባው ጥንቃቄ

ሸዋዬ ለገሠ Shewaye Legesse