DiscoverDW | Amharic - Newsቱርክ ፤ ከርዕደ መሬቱ ቀውስ ባሻገር
ቱርክ ፤ ከርዕደ መሬቱ ቀውስ ባሻገር

ቱርክ ፤ ከርዕደ መሬቱ ቀውስ ባሻገር

Update: 2023-02-13
Share

Description

«እንዳልነበርን ሆን» «በፍጹም ጠፋን » አስቡት « እናቴን አባቴን ሙሉ 12 ቤተሰቦቼን »





ይህ እናት እና አባቱን ጨምሮ 11 ቤተሰቦቹን በአንዲት ቅጽበት በሞት የተነጠቀ ሶሪያዊ ነው። የሆነው ሁሉ ህልም የሚመስል፤ ለማመን የሚከብድ፣ ነገር ግን የማይመለስ ፣ ልብ ሰባሪ አሰቃቂ አደጋ ። ሙሉ ቤተሰቡን ያጣውን ወጣት ጋዜጠኛው ሲጠይቀው በተሰበረ ልቡ አንደበቱ እየተሳሰረ እንዲህ አለ ፤ «ከእኔ በቀር ሁሉም -ደህና ናቸው» ። እነርሱስ አለፉ ፤ እርሱስ እንደምን መቋቋም ይቻለው ይሆን ?



ቱርክ የፊታችን ግንቦት ወር ሀገር አቀፍ ምርጫ ለማድረግ ዝግጅት ላይ ነበረች ። ስድስት የፖለቲካ ፓርቲዎችን በአንድነት ያጣመረው የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች ጥምረት ገዢውን ፓርቲ ይገዳደር ይሆን ተብሎም ይጠበቅም ነበር። የሆኖ አሁን ያልተጠበቀ ዱብ ዕዳ ገጥሟታል ። ጤና ይስጥልን አድማጮች ፤ ይህ ማሕደረ ዜና ነው ።



የዛሬ ሳምንት ሰኞ ሊነጋጋ ሲል ደቡባዊ ቱርክ እና ሰሜናዊ ሶሪያ በተመሳሳይ ሰዓት በሬክተር ስኬል 7.8 እና 7.5 የተመዘገበባቸው መንትያ የመሬት መንቀጥቀጥ ሁሉንም ነገር እንዳልነበረ አደረገ። ምድር ተናጠች ። በላይዋ የነበሩትን ሕንጻዎች መሸከም ተሳናት ፤ በቅጽበት ወደ ፍርስራሽነትም ተቀየሩ ።



በአደጋው በቱርክ እና ሶሪያ የሟቾች ቁጥር እስከዚህ ዘገባ ድረስ ከ34ሺህ በላይ አሻቅቧል። ከ80 ሺህ የሚልቁት ደግሞ የተለያየ መጠን ያለው ጉዳት ደርሶባቸዋል። አደጋው የደረሰበትን ስፍራ እየጎበኙ የሚገኙት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብአዊ ረድኤት ዋና ኃላፊ ማርቲን ግሪትፊልድ የሟቾች ቁጥር ከ50 ሺ በላይ ሊሆን እንደሚችል ገምተዋል። አደጋውንም አስፈሪ ሲሉ ገልጸውታል።



« እንደሚመስለኝ በደረሰው ጥፋት የተከሰተውን ጉዳት ለመገመት እጅግ በጣም አስቸጋሪ ነው። አሁንም ድረስ በፍርስራሾች ስር ተቀብረው የሚገኙ በርካቶች ናቸው። አንድ ነገር ግን እርግጠኛ ሆኜ መናገር እችላለሁ የጉዳቱ መጠን አሁን ካለው ከእጥፍ እና ከዚያ በላይ ሊጨምር እንደሚችል ነው። በጣም አስደንጋጭ ነው።»



የሰኞ ዕለቱ የመሬት መንቀጥቀጥ በሁለቱ ሃገራት ብርቱ ጉዳት ያድርስ እንጂ ንዝረቱ አህጉር አቋራጭ እንደነበር ዘገባዎች ያመለክታሉ። ከኢራቅ እስከ ግብጽ ፣ ከሊባኖስ እስከ እስራኤል የመሬት መንቀጥቀጡ የፈጠረውን ከፍተኛ ንዝረት ካስተናገዱ ሃገራት መካከል ተጠቃሾቹ ናቸው።



ቱርካውያን የፊታችን ግንቦት ወር ሀገር አቀፍ ምርጫ ለማድረግ ቀን ቆርጠው ፤ የፖለቲካ ፓርቲዎችም የምርጫ ዘመቻ ለመጀመር የሀገሪቱን የምርጫ ቦርድ የጊዜ ሰሌዳ ይጠባበቁ ነበር። ከሁለት አስርት ዓመታት ለተሻገረ ጊዜ ከ84 ሚሊዮን በላይ ህዝብ ያላትን ሀገር በፕሬዚዳንትነት እየመሩ ባሉት ኃያሉ ታይፕ ኤርዶሃን ላይ ምርጫው የሚያሳድረው ተጽዕኖ አንድምታም ያነጋግር ነበር። አደጋው ከመከሰቱ በፊት ስለቱርክ ምርጫ በርካቶች የተለያዩ አስተያየቶችን ሲያንሸራሽሩ ነበር። በተለይ ተጣማሪ የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች በዘንድሮው ምርጫ ብቅ ማለታቸው አንዳች ለውጥ ያመጣ ይሆን ብለውም የጠየቁ አሉ። አስተያየቱን ያካፈለን በቱርክ የአናዶሉ የመገናኛ ብዙኃን ዘጋቢ ጋዜጠኛ ሳዲቅ ከድር እንደሚለው ምርጫው በሀገሪቱ ለውጥ ስለማምጣት አለማምጣቱ ለመናገር ያለው ተጨባጭ ሁኔታ አይጋብዝም።



«የቱርክ የፖቲካው ሁኔታ ተለዋዋጭ ነው። እንደዚህ አሁን በእርግጠኝነት የምንገምተው ነገር አይደለም፤ ካለው የፖለቲካ እንቅስቃሴ አንጻር። ስለዚህ እኔ አሁን ለውጥ ያመጣል አያመጣም የሚለውን ለመተንበይ ምንም ያህል በቅርበት ብከታተለውም ከፖለቲካው ተጨባች ሁኔታ አንጻር ገና ብዙ ግልጽ ያልሆኑ ነገሮች አሉ።»



እንዲያም ሆኖ ግን የስድስቱ ተጣማሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች በምርጫው መሳተፍ አስቀድሞ ከነበረው አጠቃላይ የሀገሪቱ ምርጫ ውጤት አንጻር ተጽዕኖ ሊኖረው እንደሚችል ነው ሳዲቅ የሚገልጸው።



«የቱርክ የፖለቲካ እንቅስቃሴዎች ላይ እንደምታውቀው የተለያዩ ፓርቲዎች ነበሩ ሲወዳደሩ የነበሩት እና አሁን ተጽዕኖ ከፈጠረ ራሱ ሊፈጥር ይችላል ተብሎ የተጠበቀው የስድስት ፓርቲዎች ጥምረት መመስረት ነው። የነዚህ ሰዎች ድምጽ አንድ ላይ ተጽዕኖ ፈጥሮ ለውጥ ያመጣል የሚለው ነው እንግዲህ ከባለፉት ምርጫዎች ለየት ያለነገር የሚባለው።»



የሆኖ ሆኖ በአንድ በኩል ተጣማሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ኤርዶሃንን የሚገዳደር ዕጩ ፕሬዚደንት እስካሁን አለመሰየማቸው ፤ በሌላ በኩል ባለፉት ዓመታት በሀገሪቱ ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ውስጥ ትልቅ ስም እያገኙ የመጡት እና የቀድሞው የኢስታንቡል ከተማ ከንቲባ ኤክሬም ኢማሞግሉ ሁለት ዓመት ተፈርዶባቸው ዘብጥያ መውረዳቸው ሳይበቃ ፤ ከፖለቲካው ዓለም መታገዳቸው ኤርዶሃንን ብቸኛው ፈረስ ሳያደርጋቸው እንዳልቀረ ነው የሚገመተው።



እንደዚያም ሆኖ ግን አሁን ዓለም ስለ ቱርክ የሚያወራው ስለምርጫ አልያም ስለወቅታዊው ፖለቲካ እሰጥ አገባ አይደለም። አሁን ስለቅድመ ምርጫ የውጤት አንድምታ የሚወራበት ጊዜም አይደለም ። ቱርክ ታማለች። በደቡባዊ ቱርክ የምትገኘው የጋዚያንቴፕ ከተማ የርዕደ መሬቱ ያስከተለባት ሰብአዊ እና ቁሳዊ ውድመቱ አሰቃቂነቱን ለተመለከተ በርግጥ ቱርክ ሌላ አጀንዳ የምታነሳበት ጊዜ ላይ እንዳልሆነች ይረዳል ። ከተማዋን ጨምሮ በደቡባዊ ቱርክ ከ13,5 ሚሊዮን በላይ ነዋሪዎችን በሚይዝ እና 500 ስኩዌር ኪሎሜትሮች በሚሸፍን ስፍራ አስከፊው አደጋ ብርቱ ጉዳት አድርሷል።



በአደጋው የሟቾች ቁጥር 32 ሺህ ገደማ ደርሷል። ስድስት ሺህ ገደማ ሕንጻዎችም ወደ ፍርስራሽነት ተቀይረዋል። በዚህ እጅግ ቀዝቃዛ የክረምት ወቅት በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ቱርካውያን መጠለያ አልባ ሆነዋል።



ይህ ዘገባ እስከ ተጠናቀረበት ሰዓት ድረስ ማለትም አደጋው ተከስቶ በሳምንቱ ተዓምር ያሰኙ የሕይወት አድን ተግባራት እየተከናወኑ እንደሚገኙ ዘገባዎች ያመለክታሉ። የሕይወት አድን ሠራተኞች ጨቅላ ሕጻናትን ጨምሮ ሙሉ የቤተሰብ አባላትን በሕይወት ማትረፋቸውም እየተነገረ ነው። በዕድሜ የገፉ አዛውንቶች ጭምር ከፍርስራሾች ስር ተጎትተው እየወጡ ነው።



የቱርኩ ፕሬዚዳንት ጣይብ ኤርዶሃን ሃገራቸው ከበርካታ አስርት ዓመታት በኋላ በድጋሚ ያስተናገደችውን ይህኑ አስደንጋጭ አደጋ አስመልክተው የሦስት ወራት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አውጀዋል።



«አሁን ያለው ሁኔታ ያልተለመደ እርምጃ እንድንወስድ አስገድዶናል። የመሬት መንቀጥቀጡ በተከሰተባቸው 10 ግዛቶች የአደጋ ቀጠና መሆናቸውን አውጀናል። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለማወጅም ወስነናል።»





የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብአዊ ዕርዳታ የበላይ ኃላፊ ጊሪፊዝ በአደጋው ክፉኛ የተመታችውን የቱርኳይዋ ካህራማንማርስ ከተማን ትናንት ሲጎበኙ ፤ አደጋውን የክፍለ ዘመኑ አደጋ ብለውታል። በቱርክ አንካራ በጋዜጠኝነት ሥራ ላይ የተሰማራው ኢትዮጵያዊ ሳዲቅ ከድር አደጋ ያስከተለው ድንጋጤ አሁንም ድረስ እንዳለ ይናገራል።



« ይህ አደጋ እስካሁን ድረስ አስደንጋጭነቱ ያልበረደ አደጋ መሆኑን መናገር እችላለሁ ሙሉ ለሙሉ ከዚያ ስሜት ,ልተወጣም። ሁሉም ሰው ሙሉ ትኩረቱን ወደዚያ አድርጎ እዚህ ሀገር ያለ የመንግስት ተቋማት የሰብአዊ ዕርዳታ ድርጅቶች ሁሉም ሙሉ ኃይላቸውን ተጠቅመው በቦታው እየተረባበረቡ ነው የሚገኙት።»



ቅድመ ታሪክ



ቱርክ ተመሳሳይ ጉዳት ያስከተለ የመሬት መንቀጥቀጥ አደጋ የገጠማት በጎርጎርሳዊው 1939 ዓ/ም ነበር። በወቅቱ ካሁኑ እጅጉን ተመሳሳይ የሆነ ሬክተር ስኬል የተመዘገበበት ሲሆን ከ30 ሺህ በላይ የሚሆን የሰው ልጅ ሕይወት ቀጥፏል፤ ሌሎች በርካታ ሺህዎችንም ለአካል ጉዳት ዳርጓል፤ ከፍተኛ ቁሳዊ ውድመትም አድርሷል። በጎርጎርሳዊው 1999 በኢስታንቡል እና አካባቢው የተከሰተው እና በሬክተር ስኬል 7.0 የተመዘገበበት ርዕደ መሬት ሌላው ቱርካውያን መቼም የማይዘነጉት የተፈጥሮ አደጋ ሆኖ ያለፈ የታሪካቸው አካል ነው። 17 ሺህ ያህል ሰዎችን አጥተውበታል። የዚያን ጊዜው የመሬት መንቀጥቀጥ አደጋ ጠባሳው ያልሻረላቸው ዛሬም በርካቶች አሉ። ወዳጅ ዘመዶቻቸውን ያጡበት፤ የአካል ጉዳተኛ የሆኑ ፣ ሀብት ንብረታቸው እንደ ጉም ተንኖ የጠፋባቸው በእርግጥ ቁጥርራቸው ቀላል አይደለም። በቱርክ የተከሰቱ አስከፊዎቹን የመሬት መንቀጥቀጥ አደጋዎች ጠቀስን እንጂ በሀገሪቱ በየዓመቱ ሊባል በሚችል መልኩ የተለያየ መጠን ያላቸው የመሬት መንቀጥቀጥ አደጋዎች አጋጥመዋል። የጉዳታቸው መጠንም በዚያው ልክ ነው።



ቱርክ በኤኮኖሚም ሆነ ወታደራዊ አቅሟ ጡንቻዋን እያፈረጠመች የመጣች ፤ ከዓለማችን ተጽዕኖ ፈጣሪዎች ጎራ ለመቀላቀል ደፋ ቀና የምትል ፤ በአንድም ሆነ በሌላ አጋጣሚ ከኃያላኑ ጋር ተወዳዳሪ መሆን የሚያስችላትን ሁለንተናዊ አቅሟን እያሳየች የምትገኝ ሀገር መሆኗ ይነገርላታል። ለኢስያ ፣ መካከለኛው ምሥራቅ ፣ አፍሪቃ እና አውሮጳ ስልታዊ መልክዓ ምድር መያዟ ደግሞ ከፍ እያለ ለመጣው ተጽዕኖ ፈጣሪነቷ እጅጉን ሳይጠቅማት አልቀረም።



ነገር ግን አሁን የገጠማት ሌላ ነው። በወታደራዊ አቅምም ሆነ በኤኮኖሚ ልትገዳደረው የማትችለው ኃያል እና ብርቱ ነው። ስድስት ሺህ ሕንጻዎቿ ወደ ፍርስራሽነት ሲቀየሩ ፤ የኢስከንድሩን ወደብን ጨምሮ እስካሁን በትክክል ያልተገለጸ የመሰረተ ልማት ውድመት አጋጥሟታል። እስካሁን ከወጡ መረጃዎች የከፋ የአደጋ መጠን በቀጣዮቹ ቀናት ሊሰሙ ይችላሉ ። ምክንያቱም አደጋው በደረሰበት ቅጽበት አብዛኛው ሰው ቤት ውስጥ ሊሆን የሚችልበት ሰዓት በመሆኑ ነው።



ተዓምራዊ በሆነ መልኩ ከቀናት በኋላ እንኳ ከአደጋው በሕይወት እየተረፉ ያሉ ሰዎች በደረሰባቸው አደጋ ፈጣሪን ከማማረር ይልቅ ከአደጋው ለመትረፋቸው እያመሰገኑ ከፍርስራሾች ስር ሲወጡ ይሰማሉ።



ቱርካውያን ሃይማኖተኛ ህዝቦች ናቸው የሚለው ጋዜጠኛ ሳዲቅ ከድር አደጋውን ከፈጣሪ የመጣ መዓት ነው ብለው መቀበል የፈለጉ አይመስሉም ይላል። ይልቁኑ ከአደጋው የተረፉት ስለመትረፋቸው ማመስገንን ምርጫቸው አድርገዋል።



«ያለው ስሜት የደረሰው አደጋ እንግዲህ ከሃይማኖት አንጻር እነርሱ በግልጽ የተናገሩት ያው የአምላክ ቁጣ ነው የሚል ገለጻ እንስካሁን አልሰማሁም ከእዚያ ውስጥ በሚወጡበት ጊዜ በሚድኑበት ሰዓት በቃ አምላክ ሕይወታቸውን እንደመለሰላቸው ነው። ተስፋ መቁረጥ እንደሌለባቸውም ነው ሲያሰሙ የነበሩት »



ቱርክ ከአስከፊው አደጋ በኋላ ወደ ፍርስራሽነት የተቀየሩ ሕንጻዎቿን መጠን አይታ ተፈጥሯዊ ክስተት ነው ብላ ቸል ማለት አልፈለገችም። በሕንጻ ግንባታ ላይ የተሰማሩ ተቋራጮች ለአደጋው የራሳችሁ አስተዋጽዖ አለበት ስትል ከ130 በላይ ሰዎችን በቁጥጥር ስር አውላለች። ምክንያት ደግሞ የገናባችኋቸው ሕንጻዎች ርዕደ መሬትን ጨምሮ ተፈጥሯዊ አደጋዎችን እንዲቋቋሙ አድርጋችሁ አልገነባችሁም የሚል ነበር።



በቱርክ አስከፊ ጥፋት ያደረሰው የባለፈው ሰኞ የመሬት መንቀጥቀጥ ለሶሪያም ተርፏል። ከአስርት ዓመታት በላይ ለተሻገረ ጊዜ በእርስ በእርስ ጦርነት የሚታመሰው ሰሜናዊ የሶሪያ ክፍል በርዕደ መሬቱ ብርቱ ጉዳት አስተናግዷል። በሶሪያ የደረሰው ርዕደ መሬት 4,300 ገደማ ሰዎችን ሕይወት መቅጠፉ ተሰምቷል። አደጋው በአማጽያን ይዞታ እና በመንግሥት ይዞታ ስር ባሉ አካባቢዎች በመድረሱ የተደራጀ መረጃ ማግኘት አስቸጋሪ እንዳደረገው የአሶሽየትድ ፕረስ ዘገባ ያመለክታል። ዓለም አቀፍ ግብረ ሠናይ ድርጅቶች እና ሃገራት በቱርክ እና ሶሪያ በደረሰው ቀውስ የሕይወት አድን ሠራተኞቻቸውን ከመላክ ጀምሮ የእርዳታ ቁሳቁሶችን እያደረሱ ነው። ጊዜ ጠብቆ የሚናጠው የቱርክ መልክዓ ምድር ያደረሰው አስከፊ ጥፋት ገና ተጠቃሎ አልታወቀም ። በአስከፊነቱ ግን በዓማችን ከደረሱት እንደ አንዱ ተመዝግቧል። ቱርክ በአካባቢው ከነበራት የፖለቲካ ፣ ኤኮኖሚ እና ወታደራዊ ተጽዕኖ ፈጣሪነት ባሻገር የገጠማትን የተፈጥሮ አደጋ በፍጥነት ቀልብሳ ከፊቷ የሚጠብቃትን የምርጫ ድግስ ትወጣዋለች ወይ የሚለው ጥያቄም አይቀሬ ነው። የነገን ለነገ እናቆየው፤ እኔ የዛሬን በዚሁ ላብቃ ፤ ታምራት ዲንሳ ነኝ ፤ጤና ይስጥልኝ።



ታምራት ዲንሳ



ሸዋዬ ለገሰ

Comments 
In Channel
loading
00:00
00:00
x

0.5x

0.8x

1.0x

1.25x

1.5x

2.0x

3.0x

Sleep Timer

Off

End of Episode

5 Minutes

10 Minutes

15 Minutes

30 Minutes

45 Minutes

60 Minutes

120 Minutes

ቱርክ ፤ ከርዕደ መሬቱ ቀውስ ባሻገር

ቱርክ ፤ ከርዕደ መሬቱ ቀውስ ባሻገር