DiscoverDW | Amharic - Newsየተባበሩት መንግሥታት ምክትል ዋና ጸሐፊ “ምግብ ራሱ የጦር መሣሪያ ሆኗል” ሲሉ ተናገሩ
የተባበሩት መንግሥታት ምክትል ዋና ጸሐፊ “ምግብ ራሱ የጦር መሣሪያ ሆኗል” ሲሉ ተናገሩ

የተባበሩት መንግሥታት ምክትል ዋና ጸሐፊ “ምግብ ራሱ የጦር መሣሪያ ሆኗል” ሲሉ ተናገሩ

Update: 2025-11-18
Share

Description

በዓለም ዙሪያ ረሐብ የተከሰተባቸው ቦታዎች ብለው ከተለዩ 16 ሀገራት በ14ቱ የትጥቅ ግጭት ከፍተኛ የምግብ ዋስትና እጦት እንዳስከተለ የተባበሩት መንግሥታት ምክትል ጸሐፊ አሚና መሐመድ ተናግረዋል። ባለፈው ዓመት በዓለም ዙሪያ 295 ሚሊዮን ሰዎች ብርቱ ረሐብ እንደገጠማቸው የገለጹት ምክትል ዋና ጸሐፊዋ ቁጥሩ ከቀደመው ዓመት ሲነጻጸር በ14 ሚሊዮን ከፍ እንዳለ ጠቁመዋል።



የተባበሩት መንግሥታት የጥታ ጥበቃ ምክር ቤት በጉዳዩ ላይ ትላናንት ሰኞ ባደረገው ስብሰባ አሚና መሐመድ “የምግብ ሥርዓቶች ጥቃት ሲፈጸምባቸው እና እንደ ጦር መሣሪያ ጥቅም ላይ ሲውሉ ዳፋው ዓለም አቀፍ ነው” ሲሉ አስጠንቅቀዋል። “በቅርቡ በጋዛ የሆነውን ጨምሮ ሆን ብሎ ሰዎችን በማስራብ ምግብ ራሱ የጦር መሣሪያ ሆኗል። ይህ የግብርና ሥርዓቶችን ስልታዊ በሆነ መንገድ ማውደምን ይጨምራል” ሲሉ ተደምጠዋል።



አሚና መሐመድ “የሞት አዙሪት” ሲበረታ ዓለም ረሐብን ከመግታት ይልቅ “በወታደራዊ ወጪ ላይ ኢንቨስት ማድረጉን” ቀጥሏል ሲሉ ተችተዋል። ባለፉት ዐሥርተ ዓመታት የዓለም አጠቃላይ ወታደራዊ ወጪ 21.9 ትሪሊዮን ዶላር መድረሱን የጠቀሱት ምክትል ዋና ጸሐፊዋ ረሐብ በጎርጎሮሳዊው 2030 ለማቆም የሚያስፈገው ገንዘብ በአንጻሩ በዓመት ከ93 ቢሊዮን ዶላር በታች እንደሆነ ተናግረዋል።



ጉዳዩን “እንደ አዲስ መደበኛ ሁኔታ ልንቀበል አንችልም፤ አይገባምም” ሲሉ የወተወቱት አሚና መሐመድ ረሐብ እና ግጭት ያላቸው ትሥሥር ስልታዊ የሕልውና ሥጋት ነው” ሲሉ የተባበሩት መንግሥታት የጸጥታ ምክር ቤት ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ አሳስበዋል።



የተባበሩት መንግሥታት የምግብ እና የእርሻ ድርጅት ዋና ኢኮኖሚስት ማክሲሞ ቴሬሮ ቴክኒካል ባለሙያዎችን ያካተተው ዓለም አቀፍ የረሐብ ግምገማ ኮሚቴ (FRC) ባለፈው ዓመት ሦስት የተለያዩ ወቅቶች በጋዛ እና በሱዳን ጠኔ መከሰቱን እንዳወጀ በስብሰባው ተናግረዋል። ኮሚቴው በግጭት ምክንያት ከአንድ ጊዜ በላይ የከፋ ረሐብ ተከስቷል የሚል ድምዳሜ ላይ ሲደርስ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።



ማክሲሞ ቴሬሮ “በዓለም ዙሪያ 673 ሚሊዮን ገደማ ሰዎች እንደራባቸው ወደ መኝታቸው ይሔዳሉ። በአፍሪቃ 307 ሚሊዮን ወንዶች፣ ሴቶች እና ሕጻናት በቂ ምግብ አያገኙም። በእስያ ቁጥሩ 323 ሚሊዮን ደርሷል። በላቲን አሜሪካ እና ካሪቢያን 34 ሚሊዮን ሰዎች የተመጣጠነ ምግብ እጥረት አለባቸው” ሲሉ የጉዳዩን አሳሳቢነት በአሐዝ አስደግፈው ለምክር ቤቱ አስረድተዋል።



በተባበሩት መንግሥታት የምግብ እና የእርሻ ድርጅት እና የዓለም የምግብ መርሐ-ግብር በጋራ ይፋ ያደረጉት ዘገባ በጎርጎሮሳዊው ከሕዳር 2025 እስከ ግንቦት 2026 ባለው ጊዜ የከፋ ረሐብ ሊከሰትባቸው ይችላል የተባሉ 16 ሀገራት መኖራቸውን ዐሳይቷል። በዘገባው መሠረት ስድስቱ ማለትም ሱዳን፣ ፍልስጤም፣ ደቡብ ሱዳን፣ ማሊ፣ ሔይቲ እና የመን “አስከፊ” የረሐብ ሁኔታ ሊገጥማቸው ይችላል።



የሁለቱ ተቋማት የጋራ ሪፖርት ብርቱ የምግብ ዋትና እጦት ሊባባስባቸው በሚችልባቸው አካባቢዎች ስላለው ሁኔታ ቅድመ-ማስጠንቀቂያ የሚሰጥ ነው። ይሁንና ሪፖርቱ ከፍተኛ የሆነ የምግብ ዋስትና እጦት እና ለረዥም ጊዜ የዘለቁ ቀውሶች ያሉባቸውን ሁሉንም ሀገሮች፣ ሁኔታዎች እና ግዛቶች አይሸፍንም። ኢትዮጵያ፣ ማላዊ፣ ሞዛምቢክ እና የተመረጡ የካምቦዲያ እና የካሜሩን አካባቢዎች ክትትል ሊደረግባቸው የሚገባ ተብለው የተለዩ ናቸው።



በኢትዮጵያ እንደ ካምቦዲያ እና ዌስት ባንክ ሁሉ ምን ያክል ሰዎች የምግብ እና የኑሮ መደጎሚያ ርዳታ እንደሚፈልጉ ጊዜውን የጠበቀ መረጃ የለም። ይሁንና በአማራ እና በኦሮሚያ ክልሎች በመካሔድ ላይ የሚገኙ ግጭቶች፣ በትግራይ የበረታ ውጥረት እና በሰብአዊ ርዳታ ላይ የቀጠሉ ገደቦች የምግብ ዋስትናን ማዳከማቸውን እንደሚቀጥሉ ይኸው የተባበሩት መንግሥታት ሪፖርት አሳይቷል።



ባለፈው ሚያዝያ የዓለም የምግብ መርሐ-ግብርበመካሔድ ላይ የሚገኙ ግጭቶች፣ ቀጠናዊ አለመረጋጋት፣ መፈናቀል፣ ድርቅ፣ ኢኮኖሚያዊ ድንጋጤዎች በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያንን በቂ የተመጣጠነ ምግብ እንዳያገኙ ማድረጉን አስጠንቅቆ ነበር። በድርጅቱ መረጃ መሠረት ከ10 ሚሊዮን በላይ ሰዎች በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች ረሐብ እና የተመጣጠነ ምግብ እጦት ገጥሟቸዋል።



ይሁንና የዓለም የምግብ መርሐ-ግብር ሊገባደድ አንድ ወር ገደማ በቀረው የጎርጎሮሳዊው 2025 ርዳታ መስጠት የሚችለው ለ6.8 ሚሊዮን ሰዎች ብቻ ነው። ኢትዮጵያ፣ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ፣ ሔይቲ፣ ሶማሊያ እና ሱዳን ለረዥም ጊዜ በሚቆዩ እና ተደራራቢ ቀውሶች ምክንያት ላለፉት 30 ዓመታት የውጭ ርዳታ አስፈልጓቸዋል።



አርታዒ ማንተጋፍቶት ስለሺ

Comments 
In Channel
loading
00:00
00:00
x

0.5x

0.8x

1.0x

1.25x

1.5x

2.0x

3.0x

Sleep Timer

Off

End of Episode

5 Minutes

10 Minutes

15 Minutes

30 Minutes

45 Minutes

60 Minutes

120 Minutes

የተባበሩት መንግሥታት ምክትል ዋና ጸሐፊ “ምግብ ራሱ የጦር መሣሪያ ሆኗል” ሲሉ ተናገሩ

የተባበሩት መንግሥታት ምክትል ዋና ጸሐፊ “ምግብ ራሱ የጦር መሣሪያ ሆኗል” ሲሉ ተናገሩ

Eshete Bekele