በደቡብ ወሎ ዞን ሐይቅ እና ዉጫሌ ከተሞች አቅራቢያ የተጠለሉ ተፈናቃዮች ለከፍተኛ የምግብ እጥረት ተጋልጠናል አሉ
Description
በደቡብ ወሎ ዞን ሐይቅ እና ዉጫሌ ከተሞች አቅራቢያ የተጠለሉ ተፈናቃዮች ለከፍተኛ የምግብ እጥረት ተጋልጠናል አሉ ። ተፈናቃዮቹ እንዳሉት እስከ ሰባት ወራት ልዩነት ይቀርብ የነበረው አነስተኛ መጠን ያለው ምግብ አሁን እስከ መቋረጥ ደርሷል ። በሂደት ቆይቶም ቢሆን የሚቀርበው ምግብ የተበላሸ መሆኑ ወደ ከተማ በመውሰድ ለእንስሳት መኖነት ለመሸጥ እስከ መገደድ እንዳደረሳቸውም ተናግረዋል። የዉጫሌ ወረዳ የምግብ ዋስትና ባልደረባ የተፈናቃዮቹን አቤቱታ አረጋግጠው ከአምስት ወራት በኋላ አሁን መጠነኛ ድጋፍ ማድረግ መጀመራቸውን ተናግረዋል።
ስማቸውን የማንጠቅስ ተፈናቃይ ከምስራቅ ወለጋ ተፈናቅለው ሐይቅ አካባቢ ከሰፈሩ ጥቂት ዓመታት ተቆጥረዋል። ለወትሮ ለወራት እየዘገየ ይመጣ የነበረውየምግብ ርዳታበመቋረጡ ለከፋ ችግር መዳረጋቸውን ለዶቼ ቬለ ተናግረዋል።
«ኸረ ምን አለን ብለህ ነው ? በጣም ችግረኛ ነን ። ምንም ነገር የለንም ፤ የሚሰጠንም በቆሎ ነበር፤ በአራት ወር በሦስት ወር ፣ ያንንም ደግሞ የበሰበሰ የነቀዘ፣ 2001 ዓም 2002 [የተመረተ] ነው በቆሎው ፤ በዚያ ላይ ምንም ነገር የለንም መሬት ነው የምንተኛው ፣ በጣም ችግር ላይ ወድቀናል።»
እዚያው ሐይቅ እንደሚኖሩ የነገሩን ሌላው ተፈናቃይ በአስከፊ ሁኔታ ውስጥ መኖራቸውን ቢያረጋግጥም ርዳታ ይመጣልናል የሚል ተስፋ ግን እንደሰነቁ ነው።
«ምን እናደርጋለን ? ችግር በችግር ሆነናል ። እኛ እንኳ መቼም ችግሩ ይፈታልና ፣መቼም ይህ ሁሉ ጉልበተኛ ሠርቶ ይበላል የሚል ተስፋ ነበረን ፣ የርዳታው እንኳ የሚያረካ አይደለም አልሃምዲሊላህ ተኝቶ ማደሩም አንድ ነገር ነው። »
ከኦሮሚያ ፣ ከትግራይ እና ከአፋር ክልሎች በተለያዩ አጋጣሚዎች በተቀሰቀሱ ግጭቶች ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ በሺህዎች የሚቆጠሩ ተፈናቃዮች በደቡብ ወሎ ዞን በተለያዩ የመጠለያ ጣቢያዎች ተጠልለው እንደሚገኙ ጣቢያችን ሲዘግብ ቆይቷል።
ስማቸውን የማንጠቅስ አንድ የአፋር ክልል አዳይቱ ተፈናቃይ በአምባሰል ወረዳ ከደረሱ አሁን አምስት ዓመታት ማስቆጠራቸውን ይናገራሉ ። የሰብአዊ ርዳታ እና መጠለያ ፍለጋ አስቸጋሪ ዓመታት ማሳለፋቸውን የገለጹት ተፈናቃዩ አሁን ከሱዳን ጭምር ወደ አካባቢው በርካታ ተፈናቃዮች እየደረሱ መሆናቸው ችግሮቹን እያወሳሰበው እንደሚገኝ ነው የገለጹት ።
«በዚያው እኔ በመጣሁበት 2013 ግን ከትግራይ ብዙ ማኅበረሰብ መጣ ፣ ከዚያ ከአፋርም ከኦሮሚያም መጣ ፣ አሁን እየጨመረ እየጨመረ ነው የመጣው። ከዚያ አሁን ደግሞ ከሱዳንም መጥተዋል። በጣም ብዙ ማኅበረሰብ ነው ከሱዳን የመጣው አሁን ።»
በአካባቢው የተፈናቃዮች እና ስደተኞች መጨናነቅ ራሱን የቻለ መጠለያ ጣቢያ እንዳይኖር አድርጓል የሚሉት ተፈናቃይ ፣ተፈናቃዮች የኃይማኖት ተቋማትን ጨምሮ በተበታተነ ሁኔታ ውስጥ መገኘታቸው የሰብአዊ ርዳታ ለማግኘት የሚያደርጉትን ጥረት ተስፋ አስቆራጭ እንዳደረገባቸው ነው የተናገሩት።
«በቃ ምንም መፍትሔ የለንም አሁን ፣ ብዙ ነገር ጠይቀናል ፣ መጠለያ ካምፕ ጠይቀናል ፣ ተደራጅተን ጊዜያዊ ኮንቴይነር እንኳ እንዲሰጠን ጠይቀናል ፣ መልስ ግን የለንም ። ተፈናቃዩ አሁን በሳባትም በስምንትም ወር የምትመጣውን ርዳታ እየጠበቀ መኖር ሆኗል። ተስፋ የለንም አሁን።»
በደቡብ ወሎ ዞን ውስጥ ለሚገኙ ተፈናቃዮች የሰብአዊ ርዳታ በወቅቱ ለምን ማድረስ እንዳልተቻለ ለመጠየቅ በዞኑ አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ፕሮግራም ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አሊ ሰይድ የእጅ ስልክ ላይ በተደጋሚ ብንደውልም ስልካቸው ዝግ ነው ። የክልሉ አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ኃላፊን ምላሽ ለማካተት ያደረግነ ውም ጥረት የኮሚሽነሩ ዲያቆን ተስፋው ስልክ ባለመነሳቱ ሳይሰምርልን ቀርቷል።
ነገር ግን ስማቸው እንዳያጠቀስ የጠየቁን የውጫሌ ወረዳ የምግብ ዋስትና ጽ/ቤት አንድ ባልደረባ በተፈናቃዮች የቀረበውን አቤቱታ አረጋግጠው ርዳታው ከደረሳቸው አሁን በአምስተኛው ወር ለማድረስ ጥረት እያደረጉ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ለችግሩ መንግስት ትኩረት አለመስጠቱ ነገሮች እንዲወሳሰቡ ማድረጋቸውን የሚናገሩት ባልደረባው ከተፈናቃዮች የተበላሸ ምግብ እየቀረበ ነው ለሚለው ወቀሳም ማረጋገጫ ሰጥተዋል።
«ያው የትኩረት ማነስ ነው ። መንግስት ትኩረት ሰጥቶ እየደገፋቸው አይደለም። ይህም ደግሞ የሚሰጠው ጥራቱን የጠበቀም ይሄን ያህል አይደለም፤ በቆሎ በአራትም በአምስትም ወር ነው የሚሰጣቸው።»
ከላይ የሚመጣው ብዙም መፍትሄ እየሰጣቸው እንዳልሆነ የገለጹት የአደጋ መከላከል ባለሞያው ለጊዜው እንደ መፍትሔ የወሰዱት የአካባውን ማኅበረሰብ በማስተባበር አካባቢያዊ መፍትሄ በማበጀት ላይ እያተኮሩ መሆናቸውን ገልጸዋል።
የደቡብ ወሎ ዞን ጽ/ቤት በቅርቡ በማኅበራዊ መገናኛ ገጹ ባወጣው መረጃ ለአደጋ ተጋላጭ የኅብረተሰብ ክፍሎች በኢትዮጵያ ፌደራል አደጋ ስጋት ኮሚሽን እየቀረበ ያለ የሀገር ውስጥ የበቆሎ ምርት ነው ብሏል ። አክሎም በከፊልና ሙሉ በሙሉ የተበላሸ በቆሎ እያጋጠመ መሆኑን ጠቅሷል ። የዞኑ አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና በተጨማሪም፦ለብልሽት የተጋለጠ የበቆሎ እና ሌሎች ድጋፎች መቅረብ እንደሌለባቸውና ከቀረቡም ለተጠቃሚዎች እንዳይሰራጭ ለወረዳዎችና ለአመልድ ሠራተኞች መረጃ እያደረሰ እንደሚገኝ ዐስታውቆ ነበር።
ታምራት ዲንሳ
ማንተጋፍቶት ስለሺ
























