DiscoverDW | Amharic - Newsውጥረት ያልተለየው የአፍሪቃ ቀንድ ወቅታዊ ኹኔታ
ውጥረት ያልተለየው የአፍሪቃ ቀንድ ወቅታዊ ኹኔታ

ውጥረት ያልተለየው የአፍሪቃ ቀንድ ወቅታዊ ኹኔታ

Update: 2025-12-15
Share

Description



በአፍሪቃ ቀንድ ቀጣና ውስጥ ለሚኖሩ በመቶ ሚሊዮኖች ለሚቆጠሩ ሕዝቦች አለመረጋጋት ሩቅ፣ ደግሞም ረቂቅ ወይም ግራ ገብ ፅንሰ-ሀሳብ አይደለም። የዕለት ተዕለት እውነታ እንጂ። ከተፈጥሮ - ድርቅም፣ ጎርፍም፤ ከሰዎች መስተጋብር ጦርነት፣ የአስተዳደር ዘይቤ ጉስቁልና አልነው የፖለቲካ ትድድር ብልሹነት የሚወልደው ውስጣዊ ቀውስ፣ የምጣኔ ሐብት ውድቀት አለያም ድቀት መታወቂያ ሆኖ ቀጥሏል። በዚህም አያበቃም፤ ይልቁንም በወታደራዊ ኃይል የተደራጁ ፉክክሮች የሚታመሰው አካባቢ፣ በውጪ ረጃጅም ጣልቃ ገብ የእጅ አዙር ግጭጦች መታመስ ዕጣው የሆነበት ስያሜያቸውን እና ሥመ - መንግሥታቸውን አንድም ፌዴራል፣ ዴሞክራቲክ ደግሞም ሪፑብሊክ እያሉ የሚያሞካሹ ግብራቸው ግን ለአድማጭ ሚዛን የሚተው ሀገራት መገኛ ክፍለ ዓለም አድርጎት ዘልቋል።







የአፍሪቃ ቀንድ አካባቢ ጉልህ ተቃርኖዎች





የአፍሪቃ ቀንድ ቁልፍ አልያም ስልታዊ አቀማመጥ ላይ የሚገኝ ነው። ያም ሆኖ ግን ሥር በሰደደ አለመረጋጋት ይታወቃል። በዓለም ላይ እጅግ አስፈላጊ ከሆኑት የባሕር መስመሮች ወይም ኮሪደሮች ማለትም የቀይ ባሕር–ባብ ኤል-ማንደብ ወሽመጥ ላይ መገኘቱ ቁልፍ ሲያስብለው፤ በፖለቲካ ያልተረጋጋ እና ግጭት ከሚፈጠርባቸው አካባቢዎች አንዱ መሆኑ ነው - ያለመረጋጋት ምሳሌ ያደደገው። በቀጣናው የሚስተዋለው ተቃርኖ ከዚህም ያልፋል። ኢትዮጵያ እና ደቡብ ሱዳን የትላልቅ ወንዞች ባለቤት እና ከፍተኛ የዝናብመጠን የሚያገኙ ገራት ቢሆኑም ደካማ የውኃ አያያዝ ያለበት እና የአየር ንብረት ለውጥ ተጋላጭነቱ ለተደጋጋሚ ድርቅ የዳረገው ነው። የአፍሪቃ ቀንድ ጠንካራ ብሔራዊ ስሜት ያላጣ ይሁን እንጂ በሌላ ጎኑ ሃይማኖትን፣ የጎሳ ማንነትን ያጎሉ ውስጣዊ ክፍፍሎችም የማይለዩትና በዚህም ምክንያት የማዕከላዊ መንግሥታትን የአንድነት ጥረት ማዳከማቸውን የቀጠሉበት እውነት ያልተለየው ነው።





ከፍተኛ የወጣቶች ቁጥር ያለው ሆኖ ሳለም የሥራ አጥነትት ምጣኔው ሽቅብ የወጣበት መሆኑ የሚካድ አልሆነም። ቀጣናው መለያው ከዚህም ይሻገራል። ተፈጥሯዊ የባህል አንድነት ያለው ሆኖ ሲያበቃ የፖለቲካ መከፋፈል የሚያምሰው ቀጣና ጭምር ነው። የአካባቢው ሕዝቦች በታሪክ፣ በሃይማኖት፣ በቋንቋ እና በንግድ መስመሮች የተሳሰሩ ቢሆኑም ከላይ እንደጠቀስነው የፖለቲካ ሥርዓታቸውና ትብብራቸው በእጅጉ የተከፋፈለ እና ልዩነት የጎላበት ነው። ስማቸውን ትተው ሙያዊ ትንታኔ የሚሰጡን የዓለም አቀፍ ግንኙነት ተንታኝ በዚህ ተቃርኖ ይስማማሉ።

«የምሥራቅ አፍሪካ የምንለው ከባድ የሆነ ማኅበራዊ መቆላለፍ ያለበት፣ አንድ ሕዝብ ከሁለት ከሦስት ተከፋፍሎ ያለበት፣ አንዳንዴ መተማመናችንን ለማዕከላዊ መንግሥታት ሳይሆን ጎረቤት ሀገር ላለው ብጤ ብሔር የመሆን አዝማሚያ የሚታይበት፣ ከፍተኛ የሆነ ድርቅና ተፈጥሯዊ የሆነም ያልሆነም ቸነፈር የሚታይበት አካባቢ ነው።»







ሰላም በሌለበት የሰላም ስምምነቶች የሚፈረሙበት ቀጣና





የአፍሪቃ ቀንድ ቀጣና ጥቂት የማይባሉ የሰላም ስምምነቶችን አስተናግዷል። በሃገራት መካከልም ይሁን በሃገራት ውስጥ ባሉ ኃይላት እና መንግሥታት። ለዚህ ደግሞ ባለፈው ሳምንት ዓርብ ታኅሣሥ 12 ቀን 25 ዓመታት የሞላው የአልጀርስ ስምምነት ጉልህና ተጠቃሽ ነው። በኢትዮጵያ እና በኤርትራ መካከል የተካሄደውን የድንበር ጦርነት ለማስቆም በሁለቱ ሃገራት መንግሥታት መካከል የተደረገው ይህ የሰላም ስምምነት ዛሬም የመንግሥታትና የዓለም አቀፍ ተቋማት ትኩረት ያልተለየው ሆኗል። የመንግሥታቱ ድርጅት ዋና ፀሐፊ ዓርብ ዕለት የስምምነቱ ፈራሚዎች ስምምነቱን እንደገና እንዲፈጽሙ፣ አዲስ የተከሰቱ ውጥረቶች የአካባቢውን ሰላም ሊያዳክሙ እንደሚችሉ በማስጠንቀቅም «ኤርትራና ኢትዮጵያ በአልጀርስ ስምምነት ውስጥ ለተካተቱት ዘላቂ ሰላም፣ ለሉዓላዊነትና ለግዛት አንድነት ክብር እንደገና ቁርጠኛ እንዲሆኑ፣ መልካም የጎረቤት ግንኙነት ለመገንባት የሚደረጉ ጥረቶችን እንዲያጠናክሩ» ማሳሰባቸው ለተጠቀሰው አካባቢው ላልተላቀቀው ተቃርኖ ማሳያ ነው። የሁለቱ ሃገራት በጎርጎሪዮሳዊው 2018 ዐይን ገላጭና ብዙ ተስፋን ፈንጥቆ የነበረው ፈንቅሎ የወጣ በጎ መቀራረብ እና ስምምነት፣ የሱዳንና የደቡብ ሱዳን የሰላም ስምምነት ጥረቶች፣ የሶማሊያን መንግሥት የመገንባታ ሂደቶች ቢኖሩም እነዚህ ስምምነቶች ባለመተማመን እና ተግባራዊ ርምጃ እጦት ምክንያቶች ዘላቂ መረጋጋትን ማዋለድ አልቻሉም።



የአፍሪካ ቀንድ ስንል በዋናነት የ ኢትዮጵያ ፣ የሱዳን፣ እና የኤርትራ ዲፕሎማሲያዊ፣ ፖለቲካዊ እና ማኅበራዊ ጉዳይ ማለታችን ነው የሚሉት የዓለም አቀፍ ጉዳዮች ተንታኙ፤ ክፍለ አሕጉሩ ከአሜሪካ፣ ከቻይና፣ ከአውሮፓ ሃገራት፣ ከጃፓን እና ከሌሎችም ኃያላን የጦር ሰፈሮች መነኻሪያና መሻኮቻነቱ ባሻገር ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ቱርክን ጨምሮ የሳውዲ አረቢያ፣ የቃጣር፣ የተባበሩት አረብ ኢሚሬቶች እና የግብጽ አዳዲስ ፍላጎቶቻታቸውን ይዘው መምጣት፤ ተጽዕኖም የማሳደር ኹኔታ ከአካባቢው ሃገራት የራሳቸውን የውስጥ ደህንነት ማረጋገጥ ያለመቻል ችግር ጋር ተዳምሮ የቀጣናውን ከቀውስ አዙሪት የመውጣት ዕድሉን አሳጥቶታል።





«እንግዲህ ሌላው አዲስ እየመጣ ያለው ጉዳይ የግብጽ ወደ ቀጣናው በከፍተኛ ደረጃ መምጣት ነው። እንግዲህ በቅርቡም እንዳየነው ከጅቡቲም ጋር፣ ከሱማሌ ጋር፣ ምናልባት በቅርቡ ደግሞ ከኤርትራም ጋር ወደ ወታደራዊ ስምምነት፣ ከፍተኛ ወደሆነ የዲፕሎማቲክ ግንኙነት ከፍ ሊል የሚችል አዝማሚያ እያየንበት ነው ያለነው።»







ተጨማሪ የውዝግብ ማነሻ የሆነው የባሕር በር ጉዳይ





ኢትዮጵያ የዚህ አካባቢ ትልቅ ሀገር ናት። በጥቂት መመዘኛዎች። ያም ሆኖ የወጪ ገቢ ንግድ በሯ በትንሿ ግን ቁልፍ በሆነችው ሀገረ ጅቡቲ ላይ የተንጠለጠለ ሆኗል። ኢትዮጵያ እና ኤርትራ የ2018ቱ (በጎርጎሪዮሳዊ የዘመን ቀመር) መልካም ግንኙነታቸው ሻክሮ ከሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት፣ ይበልጡኑ የኢትዮጵያ መንግሥት እና ሕወሓት ከተፈራረሙት የፕሪቶሪያው ዘላቂ ግጭት የማቆም ስምምነት በኋላ ውጥረት ውስጥ ከመግባታቸው በላይ ኢትዮጵያ የባሕር በር የማግኘቱን ጉዳይ ይፋ አድርጋ፣ የያዘችውም አቋም «የሕልውና» መሆኑን ፈርጠም ባለ ኹኔታ ስታስታውቅ ኤርትራ ጉዳዩን አጥብቃ በብርቱ ነቅፋለች። ይህም ብቻ አይደለም። ምንም እንኳን በአንካራው ስምምነት ቢረግብም ኢትዮጵያ ከራስ ገዝ ሶማሊላንድ ጋር የባሕር በር ለማግኘት አድርጋው የነበረው ግን ያልተሳካው የመግባቢያ ስምምነት ፊርማ የባሕር በርን በፍትኀዊነት መጠቀም ካልተቻለ በዚህ ቀጣና ይህ የተፈጥሮ ሐብት ሌላ የውጥረት ምንጭ መሆኑ እንደማይቀር በጉልህ ታይቷል። የፕሮፌሰር መስፍን ወልደ ማርያም መታሰቢያ ፋውንዴሽን ከትናንት በስተያ «አደጋ ያንዣበበት የአፍሪካ ቀንድ እና እንደምታው» በሚል ባዘጋጀው ውይይት ላይ የተሳተፉት የሕግ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ባለሙያ የሆኑት አቶ ባይሳ ዋቅዎያ ኢትዮጵያ ካላት ታሪካዊ እና ሌሎች ታላቅ አቅሞች አንፃር በአካባቢው የበኩርነት ሚና ሊኖራት የሚገባ መሆኑን ጠቁመዋል።

«ለእኔ ትልቁ አደጋ ዛሬ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው በኢትዮጵያ እና በኤርትራ መካከል ያለው ወዳጅያዊ ያልሆና ግኑኝነት ነው። ይሄ ወደ ትልቅ ጦርነት ሊያስባን ይችላል። የሕዝብ ሳይሆን የመንግሥታቱ ጦርነት ነው። ይሄ ጦርነት ከተጀመረ ደግሞ አውዳሚ ነው የሚሆነው። የተፈለገውን ጥቅምም አያስገኝም። ይህ ማለት ኢትዮጵያ ወደብ አያስፈልጋትም፣ ያለ ወደብ መኖር እንችላለን ከሚለው ከሚለው ሀሳብ ተነስቶ ሳይሆን ወደብ እጅግ በጣም ያስፈልጋታል።»





የጦርነት ወይም የግጭት ሥጋት ያጠላበት የአፍሪቃ ቀንድ





የአፍሪቃ ቀንድ አካባቢ በእነዚህ እና በሌሎች ምክንያቶች ወደለየለት ጦርነት ውስጥ እንዳይገባ ሥጋት አልተለየውም። ሱዳን በእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ ወድቋል። የኤርትራው ፕሬዝዳንት ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም እንዲሁም ፍላጎት ውጪ ይቆማሉ ወደሚባሉት ግብጽ እና ሳውዲ አረቢያ ተጉዘዋል። እንዲያም ሆኖ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር የምሥራቅ አፍሪካ አማካሪ ጌታቸው ረዳ በሁለቱ ሃገራት መካከል ጦርነት ይነሳል የሚል ግምገማ እንደሌለ አልጀዚራ ላይ ባደረጉት ሙግት አረጋግጠዋል። የጦር ኃይሎች ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ሰሞኑን «ታሪካዊ ጠላት» ያሉት በስም ያልጠቀሱት ሀገር «ከጀርባችን በፍፁም ሊወርድ አልቻለም» ብለዋል። በኬንያ የኢትዮጵያ አምባሳደር ባጫ ደበሌ በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት በተላለፈ መልዕክታቸው የኢትዮጵያ የባሕር በር የማግኘት ጉዳይ አይቀሬ መሆኑን አስረግጠው ተናግረዋል።





«ሀገርን እና መንግሥትን መለየት አለብን» የሚሉት የሕግ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ባለሙያው አቶ ባይሳ ዋቅዎያ ወቅታዊው የኢትዮጵያ እና የኤርትራ መንግሥታት ግንኙነት ጤናማ ባይሆንም «ጉልበት፣ ጠላትነት» ለታላላቅ መንግሥታትም አልበጀም ሲሉ ሰላማዊ አማራጮችን ማየቱን ይመርጣሉ።





መንግሥታት የሌላ ሀገር አማጽያንን የሚያግዙበት ቀጣና





የአፍሪቃ ቀንድ ቀጠና ያለበት ሥነ ምኅዳራዊ ወይም ክፍለ ዓለማዊ ሁኔታ የምእራቡ ዓለም የፀጥታ ፍላጎት ብቻ የሚጎላበት ሳይሆን የእስላማዊ አክራሪ ቡድኖች መፈልፈያ መሆኑ ትኩረትን ሳቢ ያደርገዋል። የአካባቢው ሃገራት መንግሥታት ነፍጥ ያነሱ ታጣቂዎችን በስንቅም፣ በትጥቅም፣ ከለላ በመስጠትም የማገዝ ዝንባሌያቸው ግን ዛሬም የቀጠለ የቀንዱ ሥጋት ሆኗል። የዓለም አቀፍ ጉዳዮች ተንታኙ ይህንን በዝርዝር ያስረዳሉ።





«የኤርትራን መንግሥት እጥላለሁ ብሎ ትጥቅ ያነሳ ወታደራዊ ቡድን በኢትዮጵያ ውስጥ ብዙ ሲንቀሳቀስ ሰምተን አናውቅም። አሁን ግን እየመጡ ነው። አብዛኛዎቹ ደግሞ የኢትዮጵያ ትጥቅ ያነሱ ተቃዋሚዎች በኤርትራ ይታገዙ እንደነበረ የምናውቀው ነው።»





እኒህ ባለሙያ እንደሚሉት የምዕራቡ ዓለም ሃገራት ለቀጣናው ሃገራት የውስጥ ግጭት ብዙም ትኩረት ሰጥተው የሚያዩት ላይሆን ይችላል። ይህ ሲባል ግን በሃገራት መካከል ጦርነት እንዲቀሰቀስ ይፈልጋሉ ማለት አይደለም።







አዳዲስ መንግሥታትን የመመሥረቱ ሌላኛው የቀጣናው ሥጋት





የፕሮፌሰር መስፍን ወልደ ማርያም መታሰቢያ ፋውንዴሽን ቅዳሜ ዕለት «አደጋ ያንዣበበት የአፍሪካ ቀንድ እና እንደምታው» በሚል ባዘጋጀው ውይይት ላይ የተሳተፉት ሌላኛው ባለሙያ አቶ ዩሱፍ ያሲን የአፍሪቃ ቀንድን «በተለያዩ ምክንያቶች የመገንጠል እና ነፃ መንግሥት የመመሥረት ፍላጎትና ትግል ያስተናገደ» ሲሉ ይገልፁታል። ባለፉት ሦስት ዐሥርት ዐመታት ውስጥ ብቻ ኤርትራ እና ደቡብ ሱዳን ነፃ መንግሥታት መመሥረታቸውን ያስታወሱት አቶ ዩሱፍ በሌሎች የአፍሪቃ አካባቢዎች ባልታየ ኹኔታ በአፍሪቃ ቀንድ አሁንም «አዳዲስ መንግሥታት ለመመስረት የሚታዩ ጅማሮዎች አሉ» በማለት ደቡብ ሱዳን ዕጣ-ፋንታ አስፈሪ መሆኑን፣ ሶማሊያ አንድ ሁነኛ ማዕከላዊ መንግሥት የመመስረት ጥረቱ አልሳካ እንዳለው እና «ሀገሪቱ ገና ወደ 5/6 ፍንካች አናሳ መንግሥታት የመመስረት ጉዞ ተያይዛለች» ሲሉ ጁባላንድ፣ ፑንትላድ፣ ሶማሊላንድ ይህንን ዱካ እየተከተሉ መሆናቸውን ጠቅሰዋል። በሌሎች የቀጣናው ሃገራት ተፈንካች (Breakaway) መንግሥታትን የመመስረት ጉዳይ ቀጣይ ያንዣበበ አደጋ ይመስላል ብለዋል።



የማያቋርጥ ፉክክር ውስጥ ያለው የአፍሪቃ ቀንድ





ምሥራቅ አፍሪካ ኢጋድ የተባለ ክፍለ አሕጉራዊ የልማት ድርጅት አለው። ግን ጠንካራና ግቡን የመታ ነው ለማለት አያስደፍርም። ትብብርን ያበረታታል፣ ሃገራቱን በልማት፣ በሰላም ያስተሳስራል ቢባልም ኤርትራ ድርጅቱ ሚናውን እና ሕጋዊ ኃላፊነቱን መወጣት የተሳነው መሆኑን በመግለጽ ባለፈው ሳምንት ከአባልነት ራሷን አግልላለች። የዚሁ ድርጅት አባል ሃገራት በተደጋጋሚ በውክልና ጦርነቶች፣ በድንበር ግጭቶች እና በዲፕሎማሲያዊ ውጥረቶች ውስጥ ሲሳተፋም ተስተውሏል፣ ዛሬም ይሄው ሀቅ ቀጥሏል። የፕሮፌሰር መስፍን ወልደ ማርያም መታሰቢያ ፋውንዴሽን ባዘጋጀው ውይይት ላይ የተሳተፉት የሕግ ባለሙያው ዶክተር አደም ካሴ በአካባቢው የሰላም፣ የልማት እና የዕድገት ዕድል የሚመጣበትን አማራጭ ጠቁመዋል።





«በአካባቢው ባሉ አገሮች ያለውን ግንኙነት ለመቀየር ከታሰበ በውስጥ ከአምባገነንነት ከላይ ወደ ታች በሚወስድ ሳይሆን በአንጻራዊነት ዲሞክራሲያዊ የሆነ ሥርዓት መፍጠር ያስፈልጋል። ያ እስካልተፈጠረ ድረስ በአገሮች መካከል ያለው ግንኙነት ጥሩ ይሆናል ብሎ ማሰብ ልፋት ነው።»





የአፍሪካ ቀንድ ዘርፈ ብዙ ቀውስ የተፈጠሩ ምርጫዎች፣ ውሳኔዎች፣ የተዘነጉ ፍላጎቶች እና የውጭ ግፊቶች ውጤት ነው። መልካም አስተዳደር፣ ተጠያቂነት፣ ክልላዊ ትብብር እና ውሕደት፣ የውክልና ግጭት ብሎም ፖለቲካ እስኪቀር ድረስ ግን አለመረጋጋትና ቀውስ የቀጣናው እውነታ ሆኖ የሚቀጥል ይመስላል። ይህን ለማስወገድ አንዱ ሌላውን ለመጣል የሚያደርገውን ጤናማ ያልሆነ ፉክክር በማቆም፣ በቅንነት መወያየት፣ ችግሮችን ከኃይል አማራጭ ይልቅ በሰላም፣ በትብብርና በሰጥቶ መቀበል ለመፍታት በቁርጠኝነት መንቀሳቀስ ለሁሉም የሚበጅ ምርጫ ይሆናን።



ሰሎሞን ሙጬ



ሸዋዬ ለገሠ

Comments 
In Channel
loading
00:00
00:00
x

0.5x

0.8x

1.0x

1.25x

1.5x

2.0x

3.0x

Sleep Timer

Off

End of Episode

5 Minutes

10 Minutes

15 Minutes

30 Minutes

45 Minutes

60 Minutes

120 Minutes

ውጥረት ያልተለየው የአፍሪቃ ቀንድ ወቅታዊ ኹኔታ

ውጥረት ያልተለየው የአፍሪቃ ቀንድ ወቅታዊ ኹኔታ

ሰለሞን ሙጬ