የምሥራቅ ኢትዮጵያ የጸጥታ የጋራ ግብረ ኃይል ዘመቻ
Description
የምስራቅ ኢትዮጵያ የጸጥታ የጋራ ግብረ ኃይል ዘመቻ
የምሥራቅ ኢትዮጵያ የጸጥታ ግብረ ኃይል በድሬደዋ፣ በሶማሌ ክልል እና በምሥራቅ ሐረርጌ ሲንቀሳቀሱ ነበር ያላቸውን የኦነግ ሸኔ ያላቸው ራሱን የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት እያለ የሚጠራው ቡድን 43 አባላት መግደሉን አስታውቋል። ግብረ ኃይሉ በዘመቻው ከገደላቸው የቡድኑ አባላት በተጨማሪ 23 ታጣቂዎች መማረኩን ግብረ ኃይሉን ወክለው የድሬዳዋ ከተማ ፖሊስ አዛዥ ኮሚሽነር ዓለሙ መግራ ተናግረዋል።
ኮሚሽነሩ እንዳሉት ቡድኑ ካለፈውመስከረም ወርጀምሮ በኢንዱስትሪ ተቋማት ላይ ጥቃት ለማድረስ አቅዶ በምዕራብ ሐረርጌ በኩል አቋርጦ ነው ወደ ክልሉ ሰርጎ የገባው።
ግብረ ኃይሉ የመከላከያ ሠራዊትን ጨምሮ ሰባት የጸጥታ ኃይሎች ማስተባበሩን የገለጹት ኮሚሽነር ዓለሙ በቡድኑ ላይ «የማያዳግም» ያሉት አጠቃላይ ርምጃ መወሰዱን ለድሬዳዋ ከተማ ቴሌቪዝን በሰጡት መግለጫ አመልክተዋል።
«በዚሁ መሠረት 43 የጠላት ኃይል ተገድሏል። ከዚህ 43 ውስጥ ዋናው መሪ ጃል ሀረርጌ ወይም ኢት መሪ እርምጃ ተወስዶበታል ፤ሞቷል። ሌሎቹ ሁለት አመራሮች ደግሞ የርሱ ምክትሎች ጃል ቦባስ እና ጃል ራሳ ፤ጃል ቦባስ ተመትቶ የተያዘ ሲሆን ጃል ቦባስ ተማርኳል። ሃያ አምስቱ የተማረኩ እና እጅ የሰጡ አሉ ማለት ነው።»
የምሥራቅ ኢትዮጵያ የጸጥታ የጋራ ግብረ ኃይል አከናወንኩ ባለው በዚሁ ዘመቻ ከግብረ ኃይሉ ወገን ስለደረሰ ጉዳት ኮሚሽነር ዓለሙ በመግለጫቸው አላነሱም።
ነገር ግን በታጣቂ ቡድኑ ላይ ተወሰደ በተባለው በዚሁ ርምጃ ከተገደሉ እና ከተማረኩ ታጣቂዎች በተጨማሪ የታጣቂ ቡድኑ ይጠቀምባቸው የነበሩ የጦር መሣሪያዎች መማረካቸውን ኮሚሽነሩ ተናግረዋል።
«በአጠቃላይ እዚህ የገባ ጠላት ወጥቷል ማለት አይቻልም። ወደ 68 ክላሺንኮቭ ጠመንጃ ፣ አንድ ጂኤም ሦስት፣ ስምንት ቦምቦች ፣ በጣም በርካታ ቁጥር ያላቸው ጥይቶች ፣ እና የወገብ ትጥቆች የተያዙበት ሁኔታ ነው ያለው ማለት ነው።»
የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት መልስ አልሰጠም
በምሥራቅ ኢትዮጵያ በድሬ ዳዋ ከተማ እና በአካባቢው ባሉ ክልሎች ይንቀሳቀሳል በተባለው የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት አባላት ላይ የመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች ወሰዱ ስለተባለው ጥቃት እና ዘመቻ ብሎም ስለደረሰው ጉዳት ማረጋገጫ ለማግኘት ለኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ዋና አዛዥ አማካሪ አቶ ጂሬኛ ጉደታ በተንቀሳቃሽ ስልካቸው ላይ ላቀርብንላቸው ጥያቄ ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ሰዓት ድረስ መልስ አላገኘንም።
በኦሮሚያ ክልል በተለያዩ አካባቢዎች የሚንቀሳቀሰው ራሱን የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት እያለ የሚጠራው እና መንግሥት ሸኔ ብሎ የሚጠራው ቡድን ከመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች ጋር የሚያደርገው ዉጊያ አሁንም እንደቀጠለ ነው።
የፌዴራል መንግሥት የቡድኑ ዋና አዛዥ ጃል መሮ ወይም ኩምሳ ዲሪባ ከሚመሩት ተደራዳሪ ቡድን ጋር ከአንዴም ሁለቴ በታንዛንያ ያደረጉት ድርድር ፍሬ ሳያፈራ መቅረቱ ይታወሳል።
ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢe ስለመንግስታቸው ዝግጁነት ያሉት
ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አህመድ ዛሬ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች መልስ በሰጡበት ወቅት መንግሥታቸው ለሰላም ንግግሮች አሁንም በሩ ክፍት እንደሆነ ነው የተናገሩት።
« እኛ አሁንም ክፍት ነው ለመወያየት ፤ ማንም ሰው በሰላማዊ መንገድ ሕግ እና ስረዓት አክብሮ የሚመጣ ከሆነ ለመታረቅ አይደለም አብረን ለመስራት ዝግጁ ነን። አሳይተናል ሁለት ሦስት ጊዜ ፤ ገናኮ ይሄ ለውጥ መጥቶ በማግስቱ ሁላችሁም ግቡ አይደል እንዴ ያልነው ማን ቀረ ከዓለም»
እንዲያም ሆኖ ለሰላም እና ለመነጋገር መንግሥታቸው ዝግጁ መሆኑን የገለጹት ጠቅላይ ሚንስትሩ ከታጣቂ ቡድኖች ጋርበንግግር ሊፈቱ የማይችሉ ያሏቸው ነባር ችግሮች መኖራቸውን ግን አልሸሸጉም ። ምንም እንኳ ለእነዚሁ ለንግግር ምቹ ያልሆኑ ላሏቸው ጉዳዮች ሌላ የመፍትሄ መንገድ መኖሩን ቢያመላክቱም።
« ሁለተኛ ነባር ችግሮች አሉ ። በእኛ ውይይት የማይፈቱ ፤ ከሸኔዎች ጋር ብንወያይ የማይፈታ ፤ ለዚህ ደግሞ ኢንክሉሲቭ ናሽናል ዲያሎግ እናድርግ። ችግር ካለ እንደ ሀገር እንምከር እና እንፍታ ። ሕገ መንግሥት ይቀደድ ፣ ባንዲራ ይቀደድ ፣ ኢትዮጵያ ትቀደድ የምትሉ ሰዎች በእናንተ ፍላጎት ማድረግ አንችልም ፤ እንወያይ ፣ ሕዝብ ይወስን ነው ያልኩት፤»
በአማራ እና በኦሮሚያ ክልሎች አንዳንድ አካባቢዎች በታጣቂዎች እና በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች መካከል የሚደረጉ ግጭቶች አሁንም በቀጠሉበት ወቅት አንጻራዊ የጸጥታ መረጋጋት የነበረው ምሥራቃዊ የሀገሪቱ ክፍል ከአዲሱ የኢትዮጵያ ዓመት በኋላ የጸጥታ ስጋቶች ጎልተው እየተሰሙበት ነው።
የጋራ ግብረ ኃይሉ ቃል አቃባይ ኮሚሽነር ዓለሙ እንዳሉት ታጣቂ ቡድኑ ቀደም ሲል ሁለት የፖሊስ መኮንኖችን ጨምሮ በጸጥታ ኃይሎች እና ሰላማዊ ሰዎች ላይ ግድያ ፈጽሟል።
ግብረ ኃይሉ በምስል አስደግፎ ላቀረበው እና በዘመቻው አገኘሁ ስላለው ድል የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት እስካሁን በይፋ የሰጠው ምላሽ የለም ።
ታምራት ዲንሳ
ሸዋዬ ለገሰ























