DiscoverDW | Amharic - Newsየሱዳን ቀውስ፦ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ጫና ማሳደር ይችል ይሆን?
የሱዳን ቀውስ፦ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ጫና ማሳደር ይችል ይሆን?

የሱዳን ቀውስ፦ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ጫና ማሳደር ይችል ይሆን?

Update: 2025-12-03
Share

Description

ሐሙስ፤ ኅዳር 18 ቀን፣ 2018 ዓ.ም የተሰበሰበው የአውሮጳ ምክር ቤት ሱዳን ውስጥ የተከሰተውን ሰብአዊ ቀውስ በተመለከተ ባልተለመደ መልኩ ጠንከር ያሉ ቃላትን ተጠቅሟል ። የአውሮጳ ምክር ቤት አባላት ሱዳን ውስጥ የጦር ሠራዊቱ እና የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ (RSF) ተዋጊዎች የዓለም አቀፍ ሕግጋትን እና ሰብአዊ መብቶችን በመጻረር የፈጸሙት የዘር ማጥፋት ድርጊቶች ሊባሉ የሚችሉ መሆናቸውን ይፋ አድርገዋል ።



በእርግጥም ሱዳን ውስጥ የሰብአዊ መብት ጥሰቱ ከፍተኛ ደረጃ መድረሱ ይነገራል ። በተለይ ኤል ፋሽር ውስጥ በሺህዎች የሚቆጠሩ ጦር መሣሪያ ያልታጠቁ ሰላማዊ ሰዎች በፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ታጣቂዎች መጨፍጨፋቸው ብርቱ ቁጣ ቀስቅሶ ቆይቷል ። በእርግጥ የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ በወንጀሉ ተጠያቂ ያላቸውን አንዳንድ ታጣቂዎች በቁጥጥር ስር ማድረጉን ይፋ አድርጓል ። የሰብአዊ ቀውሱ ሁኔታ ሱዳን ውስጥ እጅግ የከፋ ደረጃ የሚባል መሆኑም ነው የሚነገረው ። ጃን ሠባስቲያን ፍሬድሪሽ ሩስት ረሐብን ለመከላከል የተቋቋመው መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት የጀርመን ክፍል ኃላፊ ናቸው ። ሱዳን ውስጥ የሰብአዊ ርዳታ የሚሹ ሰዎች ቁጥር ሠላሳ ሚሊዮን መድረሱን ይፋ አድርገዋል።



«በአሁኑ ወቅት የዓለማችን እጅግ የከፋው የሰብአዊ ቀውስጥ በተከሰተበት ሱዳን ውስጥ ነው የምገኘው ። እዚህ 30 ሚሊዮን ሰዎች የአብአዊ ርዳታ የሚያሻቸው ናቸው ። ሠላሳ ሚሊዮን ሰዎች ። የበለጠ ነገሩን እጅግ ከባድ የሚያደርገው ደግሞ፦ ከእነዚህ ሰዎች መካከል ከዐሥሩ አንዱን ብቻ ነው መርዳት የሚቻለው ። ከጀርመን እና ከሌሎች ለጋሽ አገራት የሚገኘው የሰብሰዊ ርዳታ ለማዳረስ ፈጽሞ በቂ አይደለም ።»



የአውሮጳ ኅብረት እና የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ጫና



እጅግ አስከፊው የሰብአዊ ቀውስ በአሁኑ ወቅት የሚገኘውም ኤል ፋሻር ውስጥ መሆኑን ኃላፊው አክለው ተናግረዋል ። ኤል ፋሻር በሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይል እጅ ከወደቀች ሰነባብታለች ።



የአውሮጳ ኅብረት የጦር መሣሪያዎች በአቡ ዳቢ በኩል ለፈጥኖ ደራሹ ኃይል እየተሸጡ ነው በሚል ከተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች ጋር ያለውን የነጻ ንግድ ስምምነት ማቆሙን ዐሳውቋል ። የተባበሩት አረብ ኢሚሬትስ የፈጥኖ ደራሹ ዋና ደጋፊ እንደሆነች በሰፊው ይነገራል ።ይህን አባባል የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ መንግስት በጥብቅ አስተባብሏል ።



የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ትኩረቱን ወደ ሱዳን እስኪያዞር ድረስ ሱዳኖች ከሁለት ዓመት ተኩል በላይ በዘለቀ መራራ ጦርነት ደም ተፋስሰዋል ። እናስ ታዲያ ተፋላሚዎቹ አሁን ስምምነት ላይ ለመድረስ ምን ያህል ተቃርበው ይሆን? ፍቅር ለሱዳን ጥናት እና ልማት የተሰኘው የሱዳን «ቲንክ ታንክ» ተቋም ዋና ኃላፊ አምጋድ ፋራይድ ኤልጣይብ የሚሉት አላቸው ።



«ማንኛውም የተኩስ አቁም ስምምነት እውን እንዲሆን፣ እርስ በእርስ የሚያያዙ በርካታ ሁኔታዎች አሉ ። በመጀመሪያ ለRSF እንቅስቃሴ የሚረዳ አቅርቦትን ማቋረጥ ። ሁለተኛ፣ RSF ላይ ተጨባጭ የሆኑ ሕጋዊ እና የገንዘብ መዘዞች እንደሚከተሉ የሚያሳዩ ማስፈራሪያዎች ሊኖሩ ይገባል ። ሦስተኛ፦ በተባበሩት አረብ ኢሚሬትስ ላይ የተጠናከረ፣ እውነተኛ እና ጠጠር ያለ ጫና ማድረግ ያሻል ። ዘላቂ የሆነ የተኩስ አቁም ስምምነት ለመፈጸም የሚደረግ ማንኛውም ሙከራ RSF ጭካኔውን እንዲቀጥልበት የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች ያላት ማዕከላዊ ሚና ላይ ማተኮር አለበት ።»



በቅርቡ የቀረበው የተኩስ ማዎም ስምምነት ምክረ-ሐሳብ ተተወ ማለት ነው?



የሱዳኑ የርስ በርስ ጦርነት ከተጫረ ሁለት ዓመት ከመንፈቅ አልፎት ወደ ሦስተኛው እያዘገመ ነው ። የሱዳን ጦር ሠራዊት መሪ ጄኔራል አብደል ፋታህ አል ቡርሃን በጄኔራል ሞሐመድ ሐምዳን ዳጋሎ (ሔሚቲ) የሚመራው የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ወደ መደበኛው ጦር ይቀላቀል የሚለው መዘዘኛ ጥሪ ነበር የምስቅልቅሉ መነሻ ። ለዓመታት የዘለቀው ደም አፋሳሽ ግጭትን ለመግታት ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶች በተደጋጋሚ ተከናውነዋል ። ሆኖም ግጭቱ ይበልጥ መልኩን እየቀየረ አሁን ያለበት ደርሷል ።



ዩናይትድ ስቴትስ፣ ግብጽ፣ የተባበሩት ዓረብ ኤሚሬቶች እና ሣዑዲ ዓረቢያ የሚገኙበት «የአራትዮሽ» አደራዳሪ ቡድንን ጨምሮ ከዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ሱዳን ላይ ጫናው በርትቷል ። ጄኔራል ሞሐመድ ሐምዳን ዳጋሎም ያለምንም ማቅማማት «ከውጊያ ለመቆጠብ» ቁርጠኛ መሆናቸውን ባለፈው ሳምንት መጀመሪያ ላይ አውጀው ነበር ። ሆኖም የሱዳን ጦር ሠራዊት ምዕራብ ኮርዶፋን ውስጥ በእግረኛ ጦር ሠራዊቴ እዝ ላይ ጥቃት ሰነዘረብኝ ሲል የከሰሰው የፈጥኖ ደራሽ ኃይል ተዋጊዎችን መልሶ ማጥቃቱን ይፋ ሲያደርግ ግን ውሎም አላደረም ። ለንደን የሚገኘው የሱዳን ፖሊሲ ጥናት ተቋም ናልደረባ ሊና ባድሪ የፈጥኖ ደራሹ ኃይል የተኩስ አቁሙን እቀበላለሁ ብሎ የነበረው ሊጠቀምበት ፈልጎ ነው ባይ ናቸው ።



ሱዳን የተኩስ አቁም ስምምነት በቅርቡ እውን ይሆን ይሆን?



«በእኔ እምነት፣ በእርግጠኝነት ማለት ይቻላ፦ RSF የተኩስ አቁሙን ተቀበልሁ ማለቱ ሥልታዊ ርምጃ ነው። የራሳቸውን ትይዩ መንግሥት ካቋቋሙበት ጊዜ ጀምሮ እንደ ዋና ዓላማቸው አድርገው የወሰዱት ራሳቸውን ማስተዳደር የሚችሉ አድርገው ለማቅረብ መጣሩን ነው ። እናም ይኼ ኤል ፋሸር በRSF ቁጥጥር ስር ከወደቀች በኋላ በሰላማዊ ሰዎች ላይ ለደረሰው የሰብአዊ መብት ጥሰት ግለሰቦችን ተጠያቂ እናደርጋለን ከሚለው ከቅርብ ጊዜ ባሕሪያቸው ጋር ተመሳሳይ ነው ።»



አሁን የሱዳን ጦርነት መልኩን ቀይሮ የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ የምዕራብ ዳርፉር አብዛኛ የሱዳን ክፍልን እና ደቡቡን በከፊል ተቆጣጥሯል ። የሱዳን ጦር ሠራዊት ደግሞ አብዛኛውን መአከላዊ የሱዳን ክፍል፤ ሰሜኑን እና ምሥራቁን ነው የተቆጣጠረው ። እናም በተፈጥሮ ሐብት በታደለችው ሱዳን የተኩስ አቁም ስምምነት በቅርቡ እውን የመሆኑ ነገር ብዙዎችን የሚያጠራጥር ሁኗል።



ማንተጋፍቶት ስለሺ/ ካቲ ሆልመስ



ፀሐይ ጫኔ

Comments 
In Channel
loading
00:00
00:00
x

0.5x

0.8x

1.0x

1.25x

1.5x

2.0x

3.0x

Sleep Timer

Off

End of Episode

5 Minutes

10 Minutes

15 Minutes

30 Minutes

45 Minutes

60 Minutes

120 Minutes

የሱዳን ቀውስ፦ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ጫና ማሳደር ይችል ይሆን?

የሱዳን ቀውስ፦ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ጫና ማሳደር ይችል ይሆን?

ማንተጋፍቶት ስለሺ ሥዩም Mantegaftot Sileshi