DiscoverDW | Amharic - Newsየአማራ ክልላዊ መንግሥት እና የአፋሕድ ሥምምነት ከማስረሻ ሰጤ ያለፈ ነው?
የአማራ ክልላዊ መንግሥት እና የአፋሕድ ሥምምነት ከማስረሻ ሰጤ ያለፈ ነው?

የአማራ ክልላዊ መንግሥት እና የአፋሕድ ሥምምነት ከማስረሻ ሰጤ ያለፈ ነው?

Update: 2025-12-05
Share

Description

የአማራ ክልል ርዕሰ-መስተዳድር አረጋ ከበደ ትላንት በአዲስ አበባ ቅንጡ ሆቴል ከማስረሻ ሰጤ ጋር በተፈራረሙት ሥምምምነት ከፍ ያለ ተስፋ ሰንቀዋል። በክልሉ ከሦስት ዓመታት ገደማ በፊት ጦርነት ከተቀሰቀሰ ወዲስ በፋኖ አመራርነት ስማቸው ከሚነሳ ግለሰብ ጋር ሥምምነት ሲፈረም የመጀመሪያው ነው።



በኢትዮጵያ መንግሥት የጸጥታ ኃይሎች እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል ውጊያ በሚደረግበት ወቅት ክልሉን የመምራት ኃላፊነት ከይልቃል ከፋለ የተረከቡት አቶ አረጋ ሥምምነቱ ከተፈረመ በኋላ “ተወያይተን እና ተደራድረን በክልላችን እና በሀገራችን ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ ቆርጠን ተነስተናል” ሲሉ ተናግረዋል።



የቀድሞው የተዋጊ ሔሊኮፕተር አብራሪ ማስረሻ ሰጤ ሥምምነቱን ከመፈራረማቸው በፊት ከሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴም ይሁን ከድርጅቱ አባልነት እንደታገዱ የአማራ ፋኖ ሕዝባዊ ድርጅት አስታውቆ ነበር። እስክንድር ነጋ በሰብሳቢነት የሚመሩት አፋሕድ ማስረሻ ሰጤ እና መሥፍን አባተ የተባሉ ሌላ አመራር “ከየትኛውም ተቋም ጋር ተገናኝተው በድርጅቱ ስም በግል እንዲናገሩ ውክልና ተሰጥቷቸው እንደማያውቅ” ኅዳር 20 ቀን 2018 ገልጿል።



የድርጅቱ መግለጫ ከወጣ ከአምስት ቀናት በኋላ ግን ማስረሻ በአፋሕድ ስም ሥምምነቱን ፈርመዋል። ሥምምነቱን ከፈረሙ በኋላ “ወደ ጫካ የወሰዱን የተለያዩ የሕዝብ ጥያቄዎች ነበሩ” ያሉት ማስረሻ ጥያቄዎች የሚመለሱበት የጊዜ ሰሌዳ መቀመጡን ተናግረዋል። ማስረሻ “በሒደት አሁን የሚመለሱ በአጭር ጊዜ፣ በመካከለኛ ጊዜ እና በረዥም ጊዜ የሚመለሱ ብለን በሦስት ከፍለን ተወያይተን ተስማምተናል” ሲሉ ተደምጠዋል።



ዶይቼ ቬለ በጉዳዩ ላይ የአማራ ፋኖ ሕዝባዊ ድርጅት ሰብሳቢ እስክንድር ነጋን ለማነጋገር ያደረገው ጥረት አልተሳካም። ይሁንና በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች በተሰራጨ የድምጽ መልዕክት አቶ እስክንድር አፋሕድ “ከተመሠረተበት ጊዜ አንስቶ በየትኛውም ጊዜ በየትኛውም ቦታ” ከመንግሥት ጋር ተደራድሮ እንደማያውቅ ገልጸዋል።



ሥምምነቱ የተፈረመው የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ምክትል ሊቀ-መንበር ሰልማ ማሊካ ሐዳዲ እና የምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ-መንግሥታት ድርጅት (ኢጋድ) ምክትል ዋና ጸሀፊ ሞሐመድ አብዲ ዋሬ በተገኙበት ነው። የአፍሪካ ኅብረት “የሥምምነቱን ተግባራዊነት እና በአጠቃላይ የኢትዮጵያን ሰላም ለመደገፍ ቁርጠኛ” እንደሆነ አስታውቋል። ሥምምነቱን “የደፋር እርምጃ” ያለው ኢጋድ “የቀሩት ታጣቂ ኃይሎች” ተመሳሳይ እርምጃ እንዲወስዱ ጥሪ አቅርቧል።



ሥምምነቱ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህን ጨምሮ በፌድራል መንግሥት እና በአማራ ክልል ቢወደስም የፋኖን አደረጃጀት እና ወታደራዊ እንቅስቃሴ በቅርብ የሚከታተሉ ፖለቲከኞች እና የጸጥታ ጉዳዮች አጥኚዎች ግን ውኃ የሚያነሳሆኖ አላገኙትም።



በእርግጥ ሥምምነቱን ፈረሙ የተባሉት ማስረሻ ሰጤ ያልተማከለ አደረጃጀት ያላቸው የፋኖ ኃይሎች ከመንግሥት ጋር መዋጋት ከጀመሩ በኋላ ስማቸው ከሚጠቀስ አመራሮች መካከል ናቸው።



የአማራ ፋኖ ሕዝባዊ ድርጅት ሥራ አስፈጻሚ እና የውጭ ግንኙነት ኃላፊ የነበሩት ማስረሻ “እንደ ጎጃም ፋኖ ተወካይ” ተደርገው ይቆጠሩ እንደነበር ፖለቲከኛው መስፍን አማን ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። “የጎጃም ፋኖን ከመሠረቱት፣ እንቅስቃሴውን መጀመሪያ ከመሩት ሰዎች አንዱ እሱ ነበር። በውጊያ አመራር ሰጪ ነው” ያሉት መስፍን “ትልቅ ቦታ ነበረው” ሲሉ አስረድተዋል።



ዶይቼ ቬለ ሐሳባቸውን የጠየቃቸው የሰላም እና ጸጥታ ጉዳዮች ጥናት ባለሙያ በበኩላቸው ባለፉት ሁለት ዓመታት ማስረሻ ስለሚመሯቸው ታጣቂዎች ብዛት ስለተቆጣጠሯቸው ቦታዎች ግልጽ መረጃ አለመኖሩን ገልጸዋል። በአቶ ዘመነ ካሴ የሚመራውን የፋኖ ቡድን “የሚቃወም” በምሥራቅ ጎጃም ዞን መርጡለ ማርያም አካባቢ “ደጋፊ አለኝ” ከሚል የዘለለ መከላከያ ሠራዊትን ከመሳሰሉ የመንግሥት የጸጥታ አስከባሪዎች ጋር ስላደረጓቸው ውጊያዎች ተጨባጭ መረጃ አለመስማታቸውን ስማቸውም ሆነ የሚሰሩበት ተቋም እንዳይገለጽ የጠየቁት ባለሙያ አስረድተዋል።



“ከአማራ ፋኖ ሕዝባዊ ድርጅት የትኛውን አንጃ ነው ሲመራ የነበረው? ምክንያቱም ቡድኖቹ ይታወቃሉ። ሸዋ አለ፣ የወሎ አለ፤ የጎንደር አለ። ጎጃም ላይ ያለው በጣም በጣም ትንሽ ነው” የሚሉት ባለሙያው “አለ ከተባለ” በማስረሻ ሰጤ እንደሆነ ይሞግታሉ። “በጎጃም ትልቅ ቦታ ያለው የአማራ ፋኖ ብሔራዊ ኃይል ወይም የእነ ዘመነ ቡድን ነው” በማለት አስረድተዋል።



“እጃቸውን ሰጡ የሚል መረጃ ከአምስት ቀናት ገደማ በፊት” መሰማቱን የጠቀሱት ባለሙያው ከአቶ ማስረሻ ጋር ጓደኛቸው እና የተወሰኑ ሰዎች አብረው እንደሚኖሩ ይገምታሉ።



አቶ ማስረሻ በፋኖ አደረጃጀት ውስጥ በነበራቸው ሚና ላይ በሚነሱ ጥያቄዎች ምክንያት ከአማራ ክልላዊ መንግሥት ጋር የተፈረመው “የግለሰቦች ሥምምነት ይመስላል” የሚል አቋም አላቸው። “ለፖለቲካ ጥቅም መንግሥት ሁሉንም አጋጣሚ ይጠቀማል። በዚያ ላይ ምርጫም እየመጣ ነው። እያረጋጋን ነው፤ ሰላም እያወረድን ነው” ለማለት ሊጠቀምበት እንደሚችል ያምናሉ።



“በአማጺነት ተሰማርቶ በቆየ አካል እና በመንግሥት መካከል የሚደረግ ሥምምነት ጊዜ ይወስዳል” የሚሉት ባለሙያ “መቼ ተወያዩ? ምን ያክል ጊዜ? ውይይቱን ማን ነው የመራው? ተወያዮቹስ በማን ተወከሉ?” የሚሉ ጥያቄዎች ያነሳሉ። በዚህም ምክንያት ሥምምነቱ “ውኃ የማያነሳ” እንደሆነ ተችተዋል።



አቶ ማስረሻ “እጁን ነው የሰጠው” የሚሉት አቶ መስፍን በበኩላቸው “እጁን የሰጠን ሰው የሰላም ሥምምነት ተፈራረመ ልትል አትችልም” ሲሉ ተናግረዋል።



ዶይቸ ቬለ ያነጋገራቸው ሌላ የጸጥታ እና የግጭት ትንተና ጥናት ባለሙያ “መንግሥት ለችግሩ እውነተኛ የሰላም አካሔድን እንደማይከተል የሚያሳይ ምልክት ነው” ሲሉ ተችተዋል። አቶ ማስረሻ ሥምምነቱን ከፈረሙ በኋላ በአማራ ክልል እየተካሔደ የሚገኘው ውጊያ “ቢቀጥል ከዚህ በላይ ሕዝባችን መሸከም አይችልም” ሲሉ ተደምጠዋል። አቶ መስፍን ግን የተፈረመው ሥምምነት የሚቀይረው ነገር እንደማይኖር ያምናሉ።



“አብዛኛው ፋኖ እንደዚህ አይነት ድርድር መደረጉን ልክ እኛ እዚህ ከውጪ እንደሰማንው ነው የሰማው” የሚሉት አቶ መስፍን “በጎጃም አካባቢ፣ ደቡብ ጎንደር፣ ሰሜን ሸዋ ውጊያዎች እንደቀጠሉ ናቸው። ምንም የሚቀይረው ነገር አይኖርም” ሲሉ ተናግረዋል።



አርታዒ ጸሀይ ጫኔ

Comments 
loading
In Channel
loading
00:00
00:00
1.0x

0.5x

0.8x

1.0x

1.25x

1.5x

2.0x

3.0x

Sleep Timer

Off

End of Episode

5 Minutes

10 Minutes

15 Minutes

30 Minutes

45 Minutes

60 Minutes

120 Minutes

የአማራ ክልላዊ መንግሥት እና የአፋሕድ ሥምምነት ከማስረሻ ሰጤ ያለፈ ነው?

የአማራ ክልላዊ መንግሥት እና የአፋሕድ ሥምምነት ከማስረሻ ሰጤ ያለፈ ነው?

Eshete Bekele