DiscoverDW | Amharic - Newsየኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የ520 ሚሊዮን ዶላር ስምንት ጨረታዎች ይፋ ሲያደርግ ምን እያለ ነው?
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የ520 ሚሊዮን ዶላር ስምንት ጨረታዎች ይፋ ሲያደርግ ምን እያለ ነው?

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የ520 ሚሊዮን ዶላር ስምንት ጨረታዎች ይፋ ሲያደርግ ምን እያለ ነው?

Update: 2025-11-21
Share

Description

የውጭ ምንዛሪ ግብይት በአቅርቦት እና ፍላጎት እንዲወሰን ከተደረገ ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ዶላር ለባንኮች የሚያከፋፍልባቸውን ስምንት ተከታታይ የጨረታ ቀናት በአንድ ጊዜ ይፋ አድርጓል። ከኅዳር እስከ መጋቢት በየሁለት ሣምንቱ በሚካሔዱ ጨረታዎች በአጠቃላይ 520 ሚሊዮን ዶላር ለባንኮች እንደሚያከፋፍል ባንኩ ትናንት ሐሙስ አሳውቋል።



ብሔራዊ ባንክ “የውጭ ምንዛሪ ገበያ በተረጋጋ መልኩ እንዲሔድ ቢያንስ በእኔ በኩል ያለውን ነገር መተንበይ ትችላላችሁ” የሚል መልዕክት ለባንኮች፣ አስመጪ እና ላኪዎች በአጠቃላይም ለኢኮኖሚው በማስተላለፍ “ተዓማኒነት እና ግልጽነትን” ለማስፈን የሞከረበት እንደሆነ የፕራግማ ኢንቨስትመንት አድቫይዘሪ ዋና ሥራ አስፈጻሚ መርዕድ ብሥራት ይናገራሉ።



በውጭ ምንዛሪ ገበያው “ግልጽነት እና ተገማች አሠራር ለማጠናከር” ዶክተር እዮብ ተካልኝ የሚመሩት ብሔራዊ ባንክ “በየሩብ ዓመቱ የሚደረጉ የጨረታ ግብይቶችን” እንደሚያሳውቅ ቃል ገብቷል። የፋይናንስ ባለሙያው ዶክተር አብዱልመናን መሐመድ ለኢትዮጵያ ባለሥልጣናት “ገበያው በፍጹም እንዳልጠበቁት” እየሆነ ሳይቸገሩ እንዳልቀረ ያምናሉ።



“የውጭ ምንዛሪ ተመኑ ማቆሚያው የት እንደሆነ በማይታወቅ ሁኔታ ዝም ብሎ እየጨመረ” መሆኑን የታዘቡት ዶክተር አብዱልመናን ብሔራዊ ባንክ ከዚህ ቀደም ማዕከላዊው ባንክ ያካሔዳቸው ጨረታዎች የምንዛሪ ገበያውን ማረጋጋት እንዳልተሳካላቸው አስረድተዋል።



“ይኸን ያህል የውጭ ምንዛሪ መንግሥት የሚያቀርብ ከሆነ ባንኮቹ ከሸቀጦች የወጪ ንግድ እና ከሐዋላ የሚያገኙትን የውጭ ምንዛሪ ያውቃሉ። ምን ያህል የውጭ ምንዛሪ ፍላጎት እንዳለም ያውቃሉ። ከዚያ በመነሳት የውጭ ምንዛሪ ተመናቸውን በተወሰነ ደረጃ ለማረጋጋት ይረዳል ከሚል ይመስለኛል” የሚሉት ዶክተር አብዱልመናን “ዋና ዓላማው ግን ተገማችነትን መፍጠር ነው” በማለት አስረድተዋል።



የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ “የውጭ ምንዛሪ አቅርቦትን ለማሻሻል እና የተረጋጋ ተመን እንዲኖር ለማስቻል” በየሁለት ሣምንቱ የዶላር ጨረታ ማካሔድ የጀመረው በመጋቢት 2017 ነበር። ጨረታዎቹ በሚካሔዱባቸው ወቅቶች የባንኮች እና የትይዩ ገበያው የውጭ ምንዛሪ ግብይቶች የመረጋጋት አዝማሚያ ሲያሳዩ ቆይተዋል።



ሀገሪቱ የምታገኘው የውጭ ምንዛሪ መሻሻል ቢያሳይም ችግሩ በዘላቂነት መፍትሔ ባለማግኘቱ ጨረታዎቹ ብርን ከመዳከም ሊታደጉት አልቻሉም። ባለፈው አንድ ወር ውስጥ ብቻ ብር በብሔራዊ ባንክ አመልካች ዕለታዊ የምንዛሪ ተመን መሠረት 2.9 በመቶ ተዳክሟል። የፋይናንስ እና ኢንቨስትመንት ባለሙያው አቶ መርዕድ የብሔራዊ ባንክ ይፋ ያደረጋቸው ጨረታዎች ከመስከረም ጀምሮ ሲዳከም ለቆየው ብር “መረጋጋትን ይፈጥራል” የሚል ዕምነት አላቸው።



በብሔራዊ ባንክ ፈቃድ የተሰጣቸው የውጭ ምንዛሪ ቢሮዎች ዶላር 174 ብር ገደማ ገዝተው 177 ብር ገደማ ይሸጣሉ። ይሁንና ዶላርን የመሳሰሉ የመገበያያ ገንዘቦች በሚመነዝሩበት ተመን ላይ ለመደራደር ፈቃደኛ የሆኑ ቢሮዎች መኖራቸውን ዶይቼ ቬለ ለመገንዘብ ችሏል። ለበርካታ ባለሙያዎች ከባንኮች ይልቅ የምንዛሪ ቢሮዎች ተመን ወደ ትክክለኛው የብር ዋጋ የቀረበ እንደሆነ በርካታ ባለሙያዎች ያምናሉ።



ባንኮች በአንጻሩ ሁለት ተመኖች በየዕለቱ ያወጣሉ። የውጭ ምንዛሪ ገበያውን ይመራል ተብሎ የሚታመነው መንግሥታዊው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለምሳሌ በዛሬው ዕለት ዶላር በ150 ብር ከ50 ሣንቲም ገደማ ገዝቶ 153 ብር ከ50 ሣንቲም ገደማ ይሸጣል። ይሁንና የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለደንበኞቹ ቃል በሚገባው “10 ብር ተጨማሪ ጉርሻ” ምክንያት የዶላር ምንዛሪው ወደ 163 ብር ከ50 ሳንቲም ገደማ ከፍ ይላል። የኦሮሚያ ኅብረት ሥራ ባንክ 10% ፣ አዋሽ ባንክ እና አቢሲኒያ ባንክ 2% ከዕለታዊ ምንዛሪያቸው በተጨማሪ ለደንበኞቻቸው ለመስጠት ቃል ይገባሉ።



ባንኮች ቃል የሚገቡት ጉርሻ “የሚለጥፉት ዋጋ ውስጥ ነው መግባት ያለበት” የሚሉት መርዕድ ዶላርን የመሳሰሉ መገበያያ ገንዘቦች የምንዛሪ ተመናቸው ላይ “የሚጫን ከሆነ ዋጋውን እየረባበሸ ነው” ሲሉ ተናግረዋል። መርዕድ “ጉርሻ እየተባለ ሁለት ዋጋ ሊኖረን አይችልም” የሚል አቋም አላቸው። የባንኮች ጉርሻ ከውጭ ምንዛሪ ጋር ለተያያዙ አገልግሎቶች የሚጠይቁት ክፍያ ጋር ተደምሮ በተመኑ ላይ አሉታታዊ ጫና ያሳድራል።



የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ከውጭ ምንዛሪ ጋር ለተያያዙ አገልግሎቶች የሚጠይቁት ክፍያ ከ4 በመቶ እንዳይበልጥ ቢወስንም ዋጋውን አልተመነም። “ተወዳደሩበት ነበር የተባለው። [ባንኮች] እሱንም እየተከተሉ አይደለም” የሚሉት መርዕድ “ሁሉም ባይሆኑም ባንኮች ጋር ትልቅ ችግር አለ። ይህ ነገር መታረም አለበት” ሲሉ ተናግረዋል።



ዶክተር አብዱልመናን ግን የውጭ ምንዛሪ ግብይቱ ሊረጋጋ የሚችለው ሀገሪቱ ከፍላጎቷ የሚጣጣም የውጭ ምንዛሪ ማግኘት ስትችል ብቻ እንደሆነ ይናገራሉ። “ለውጥ የሚያመጣው በቂ የውጭ ምንዛሪ ሲኖር ብቻ ነው። ሰፊ ልዩነት ካለ 520 ሚሊዮን ዶላር ከተትክም አልከተትክም ለውጥ አያመጣም” የሚል አተያይ አላቸው። “520 ሚሊዮን ዶላሩ ኢንደስትሪውን የሚያንበሸብሸው ከሆነ ለውጥ ያመጣል። ግን አይመስለኝም” የሚሉት ዶክተር አብዱልመናን “ለ31 ባንክ 520 ሚሊዮን ዶላር ምንድነው? በጣም ትንሽ እኮ ነው” ሲሉ ፋይዳው ጉልህ ሊሆን እንደማይችል አስረድተዋል።



አቶ መርዕድ ብሔራዊ ባንክ የወሰደው ርምጃ በባንኮች ላይ ተጥሎ የቆየውን የብድር ገደብ የብሔራዊ ባንክ የገንዘብ ፖሊሲ ኮሚቴ ከሚቀጥሉት ሁለት ተከታታይ ስብሰባዎች በአንዱ ሊያነሳ እንደሚችል ጥቆማ ሰጥቷቸዋል። ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ቁልፍ ማሻሻያዎች አንዱ የሀገሪቱን የገንዘብ ፖሊሲ ገበያ ተኮር ማድረግ ነው።



በዚህም መሠረት በባንክ የሥራ ዘርፍ ግልጽነትን እና የሥጋት አስተዳደርን ለማጠናከር የተዘጋጁ ባዝል አንድ እና ባዝል ሁለት የተሰኙ ዓለም አቀፍ የባንኮች ቁጥጥር ማዕቀፎች ተግባራዊ እንዲሆኑ መመሪያ አውጥቷል። መመሪያዎቹ የኢትዮጵያ ባንኮች ወደ 660,000 የሚጠጉ የብድር ውሎች ወደ ገበያ መር የወለድ ምጣኔ እንዲሸጋገሩ ያደርጋቸዋል።



የብሔራዊ ባንክ የገንዘብ ፖሊሲ ኮሚቴ በታኅሳስ አሊያም በመጋቢት በሚያደርጋቸው ስብሰባዎች “የብድር ገደቡን ሲያነሳው የውጭ ምንዛሪ ገበያው እንዳይደነግጥ” ትላንት ሐሙስ ይፋ የተደረገው የ520 ሚሊዮን ዶላር ጨረታ አስቀድሞ መልዕክት እንደሚያስተላልፍ አቶ መርዕድ አስረድተዋል።



ከባንኮች አሠራር በተጨማሪ ኢኮኖሚውን የሚጫነው የኢትዮጵያ የፖለቲካ እና የጸጥታ ሁኔታ የተረጋጋ የውጭ ምንዛሪ ሥርዓት ለመዘርጋት የሚያስችል አይደለም። “እርግጥ ነው አሁንም በሀገሪቱ አለመረጋጋት አለ” የሚሉት አቶ መርዕድ “ባልተረጋጋ ሀገር የውጭ ምንዛሪ [ገበያ] ይረጋጋል ማለት በጣም አስቸጋሪ ነገር ነው” ሲሉ ተናግረዋል።



ካፒታል ከኢትዮጵያ ማውጣት የሚቻልበት ሕጋዊ ሥርዓት አሁንም ዝግ ሆኖ መቆየቱ ሰዎች ወደ ትይዩው ገበያ እንዲያማትሩ የሚያደርግ ሌላው ፈተና ነው። የኢትዮጵያ “ካፒታል አካውንት” ዝግ ሆኖ ትይዩ “ገበያው ይጠፋል ወይም ይመነምናል ማለት በጣም አስቸጋሪ ነው” የሚሉት አቶ መርዕድ ቢያንስ “እንዴት አድርገን ብንከፍተው ጥሩ ነው?” የሚለውን ለመፈተሽ ጥናት ሊጀመር እንደሚገባ ይመክራሉ።



አርታዒ ማንተጋፍቶት ስለሺ

Comments 
In Channel
loading
00:00
00:00
x

0.5x

0.8x

1.0x

1.25x

1.5x

2.0x

3.0x

Sleep Timer

Off

End of Episode

5 Minutes

10 Minutes

15 Minutes

30 Minutes

45 Minutes

60 Minutes

120 Minutes

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የ520 ሚሊዮን ዶላር ስምንት ጨረታዎች ይፋ ሲያደርግ ምን እያለ ነው?

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የ520 ሚሊዮን ዶላር ስምንት ጨረታዎች ይፋ ሲያደርግ ምን እያለ ነው?

Eshete Bekele