በኢትዮጵያ የሰብአዊ መብት ሁኔታ ላይ የተካሄደ ውይይት
Description
በኢትዮጵያ የሰብአዊ መብት ሁኔታ ላይ የተካሄደ ውይይት
በኢትዮጵያ የሚታየው የሰብአዊ መብት ሁኔታ፣ ወደ ከፋ ደረጃ እያመራ መሆኑን የኢትዮጵያን እናድን መድረክ አስታወቀ። ተቀማጭነቱን በአሜሪካ ያደረገው፣"ኢትዮጵያን እናድን" መድረክ፣ በኢትዬጵያ የሰብአዊ መብት ሁኔታ ላይ ያተኮረ ውይይት አካሂዷል። ዶይቸ ቨለ ያነጋገራቸው፣የመድረኩ አስተባባሪ ፕሮፌሰር ጌታቸው መታፈሪያ እንደሚሉት፣ኢትዮጵያ ውስጥ የሚታየው የሰብአዊ መብት ሁኔታ፣ከዕለት ወደ ዕለት እያሽቆለቆለ መጥቷል።
በኢትዮጵያ የሰብአዊ መብቶች ይዞታ ላይ ሰሞኑን በተካሄደው መድረክ ላይ፣ ከተሳታፊዎቹ መኻከል በተለያየ አጋጣሚዎች የተመለከቱትን አሳሳቢ የሰብአዊ መብት አያያዝ ሁኔታን በማሳያነት ያቀረቡበት፣የዘርፉ ባለሙያም ገለጻ ያደረጉበት ነበር።
የጥሪ ደወል የጋዜጠኞች ሥደት እና የመብት ተሟጋች ድርጅቱ ጥሪ
የውይይት መድረኩ የጥሪ ደወል ነው የሚሉት የመድረኩ አስተባባሪ ፕሮፌሰር ጌታቸው መታፈሪያ፣ በኢትዮጵያ የሚታየው የሰብአዊ መብት ሁኔታ ወደ አስከፊ ደረጃ እያመራ መሆኑን፣ለዶይቸ ቨለ በሰጡት አስተያየት አመልክተዋል። "አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ የሚካሄደው፣ ዘር ማጥፋት ስንል በሰፊው ነው የምናየው፣ወደ እዛ እየሄደ ነው፤ሁኔታዎች እያሽቆለቆሉ ናቸው።አንድ ምክንያት ብቻ ይፈልጋል።እንድ ክብሪት ቢጫርበት፣ኢትዮጵያ ሩዋንዳ ወደ መሆን አዝማሚያ እየሄደች ነውና ከአሁኑ ይኼ የጥሪ ደወል ነው።እና ከአሁኑ የዓለም ህዝብ ሁሉ ዐውቆ ከኢትዮጵያ ህዝብ ጎን እንዲቆምና ይህን መጥፎ ውድቀት እንዲያድንና የህዝብን ዕልቂት እንዲያድን ለማድረግ ነው።"
ዛሬ ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ቀን ነው
ለዓለም አቀፉ ማኀበረሰብ የቀረበው ጥሪ
በበይነ መረብ አማካይነት የተዘጋጀው ይኸው ውይይት፣ በእንግሊዝኛ ቋንቋ የተካኼደ ሲሆን፣ይህ የኾነበት ምክንያት፣የኢትዮጵያን አጠቃላይ የሰብአዊ መብት ይዞታ ዓለም አቀፉ ማኀበረሰብ እንዲገነዘብ ለማድረግ መሆኑን አስተባባሪው ይናገራሉ። "የውጭ ሰዎች እንዲያደምጡና ያለውን የኢትዮጵያ ሁኔታ አስጊ ሁኔታ ላይ እንዳለ እንዲያውቁትና እነሱም ደግሞ አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ፣ የሰብአዊ ሁኔታ ስለሆነ፣ ሁላችንም ሰብአዊ ስለሆንን በእዛ ላይ እንዲተባበሩና ኢትዮጵያን ከጥፋት እንዲያድኗት እንዲያግዙን ለማለት ነው።በዚያ ሁኔታ በእንግሊዝኛ ቋንቋ ነበር የተካሄደው፤ ከአውሮፓ ከአፍሪቃ፣ ከአሜሪካና ካናዳ የተሳተፉበት ሁኔታ ነበር።"
በኢትዮጽያ የሚፈፀሙ ሰብአዊ መብት ጥሰቶች መጨመራቸዉ ተነገረ
የኢትዮጵያን የማዳን መድረክ ዓላማዎች
ኢትዮጵያን የማዳን መድረክ፣ ከተቋቋመ ሁለት ዓመታትን አስቆጥሯል። ፕሮፌሰር ጌታቸው፣ መድረኩ የተቋቋመበትን ዓላማ እንደሚከተለው ገልጸውልናል። "ይህን መድረክ ያቋቋምን ሰዎች፣ ምንም የፖለቲካ አቋም የሌላቸው፣ ዕውቀታቸውንና ተሞክሯቸውን ተጠቅመው፣ እቺን አገር የማዳን፣ ከፖለቲካ ውድቀት፣ከኢኮኖሚ ውድቀት ከማንነት ውድቀት እና አገሪቱ ወደ ከፋ ሁኔታ እንዳትኼድ ለመምከር የተዘጋጀ ድርጅት ነው። እና በእዛ ላይ ሰፋ ያለ፣አንድ 29 ገጽ የሚሆን ሰነድ አውጥቷል።ይህንንም ሰነድ፣ለኢትዮጵያ መንግሥት፣ለኃይማኖት ተቋማት፣ለአባ ገዳዎች እና ለሌሎችም ሁሉ ተዳርሷል።" በጉዳዩ ላይ የኢትዮጵያን መንግስት አስተያየት ለማግኘት፣ ለኮሙኑኬሽን አገልግሎት መስሪያ ቤት፣የስልክ ጥሪ ብናደርግም ለጊዜው ምላሽ አላገኘንም። ወደ ኢትዮጵያ የሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን፣በኤሜልና በስልክ ያደረግነው ሙከራም አልተሳካም።
ከዚህ ቀደም በሰብአዊ መብት ጥበቃ ላይ የሚሰሩ ሀገር በቀልና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች በሚያወጧቸው ሪፖርቶች፣ በኢትዮጵያ ዘርፈ ብዙ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች፣ሥጋቶች እና አሳሰቢ ሁኔታዎች መኖራቸውን በተደጋጋሚ መግለጻቸው አይዘጋም።
ታሪኩ ኃይሉ
አዜብ ታደሰ
ሸዋዬ ለገሠ
























