ወጣቶች መሞት እንዳለ እያወቁ ለምን በአደገኛ የጉዞ መስመር ይሰደዳሉ?
Description
ህይወት በእድል ትመራለች የሚሉት የሰሜን ወሎ ዞንወጣቶች አስቸጋሪውን እና የብዙዎቹን ህይወት የቀጠፈውን የባህር ላይ ጉዞ በየእለቱ ወደ አረብ ሀገራት እና ሌሎች የአውሮፓ ሀገሮች ለመጓዝ መዳረሻ በማድረግ በሕገወጥ መንገድ ከሞት ጋር ግብግብ ይዘው በተደጋጋሚ ይፈፅሙታል፡፡ ወጣት መካሽ ቢምረው የኑሮ ውድነት እና በአካባቢው ያለው ሰላም መደፍረስ ፣ ስራ ሰርቶ መኖር ስላላስቻለው በባህር ላይ ሲጓዙ ህይወታቸው ያለፉ ጓደኞቹን ሀዘን በቅጡ ሳይወጣ የእነርሱን መንገድ እርሱም መምረጡን ይናገራል፡፡ « የኑሮ ሁኔታው ልዩነት አለው አሁን ላይ ወጣቱም ከቤተሰቡ መቀበል እየከበደው ነው፡፡ ስራ ሊሰራ ሲል ዱላ አለ፤ ወጥቶ ለመግባት ሰላም ያስፈልጋል፤ አሁን የእኔ ሰፈር 3 ድንኳን አለ፤ ገና አልተነቀለም፤ የእኔ ወንድሞች፣ ጓደኞች ናቸው የሞቱት፣ ከመሄድ ግን ወደ ኋላ አልልም ለምን ምንም የተሻለ ነገር የለም እዚህ፡፡»
የሰላም እጦት ለወጣቶች ሰደት ምክንያት ነዉ
ሌላው የዋጃ ከተማ ነዋሪ የሆነ ወጣትም ከዚህ ቀደም በባህር ላይ ጉዞ ወደ ሳውዲ አረቢያ ቢያመራም ተመልሶ መጥቷል፡፡ አሁንም ለመሄድ ነው የሚያስበው በማዕበል ምክንያት፣ በረሃብ እና ውሃ ጥም የሞቱ ጓደኞቹን ግን ያስታውሳል፡፡ ‹‹ዋጃ ላይ በጣም አልቋል እኔም እራሴ ስደተኛ ነኝ፤ መከራ አለ፤ ተስፋ ቆርጠህ ነው የምትሄደው ከዚህ ስትወጣ ሞትን ትመርጣለህ፤ በስደት ላይ አብሮህ ያለ ጓደኛ ሲነጠልህ ታየዋለህ፤ በርሃብ፤በማዕበል፡፡››
መንግስት ትኩረት ያልሰጠዉ የወጣቶች ፍልሰት
አካባቢው በመንግስት ብዙም ትኩረት አልተሰጠውም የሚለው ወጣት አሁን በዞኑ በመንግስትና በፋኖ ኃይሎች መካከል በሚደረገው ጦርነት ተስፋ በመቁረጥ ያላቸውን ንብረት ሸጠው ወደ አውሮፓ ሀገሮች ለመሰደድ የሚሞክሩ ወጣቶች በሊቢያ በኩል ይጓዛሉ፡፡ «እዛ ሄደው ቢሞቱ ይሻላል፤ እዚህ በታጣቂ ከሚሞቱ፤ ሳውዲ አረቢያን ታያለህ እንጂ ወጣቱ ያለውን ሸጦ ወደ አውሮፓ በሊቢያ አድርገው እየሄዱ ነው፤ ነገ የሚሄዱ አምስት ልጆች ልገልጽልህ እችላለሁ፡፡›› አሁን የባህር ላይ ጉዞውን አጠናቆ በየመን ወደ ሳውዲአረቢያ ለመግባት በመጠባበቅ ላይ ያለ ወጣትም ከአስቸጋሪው የባህር ላይ ጉዞ በኋላ በበረሃ የሞቱ ኢትዮጵያዊያን በርካታ መሆናቸውን ይናገራል፡፡‹‹በስደት ዓለም ላይ ያለውን ባታየው፣ ባሰማው ነው የሚሻለው ሰንዐ ላይ የነበሩት አልቀዋል፡፡ በአንዳንድ ነገር የተያዙ ሀበሾች በድንበር የምንሰራበትን አካባቢ ሬሳ እየተራመድክ ነው ስራ የምትሰራው ሬሳ ብቻ ነው፡፡ ያልተቀበሩም አሉ፡፡››
በአንድ አለም አቀፍ የግብረ ሰናይ ድርጅት ውስጥ የሚሰሩና ለደህንነታቸው ሲባል ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ ሰራተኛም በአካባቢው ወጣቶች ተስፋ በመቁረጥ እና በጦርነቱ ምክንያት አካባቢያቸውን ለቀው እየተንቀሳቀሱ ነው ይላሉ፡፡ ‹‹በጦርነቱ ምክንያት ሰላም አለመኖሩ የስራ አጥነት በመኖሩ ሰው እየተንቀሳቀሰ ነው፡፡ ምንም ልትገድበው አትችልም፣ ተስፋ በመቁረጥ ነው፤ ይህንን አደገኛ መንገድ የሚጠቀሙት፡፡››
በሰሜን ወሎ ዞን በተለይም በቆላማ አካባቢዎች ወደ አረብ ሀገራት የሚደረግ ሕገወጥ ጉዞ እንደ ባህል ጭምርተይዞ በስፋት የሚከወን ነው ያሉት የዞኑ ምክትል አስተዳዳሪ አቶ ታምራት ንጋቱ ከ2 ዓመት በፊት በከፍተኛ ሁኔታ ሕገወጥ ጉዞው እንዲቀንስ ማድረግ ቢቻልም አሁን ግን በአካባቢው ካለ ጦርነት ጋር ተያይዞ ሕገ ወጥነቱ በርትቷል ሲሉ ይናገራሉ፡፡
‹‹ከ2ዓመት በፊት በብዙ መልኩ ቀንሰነው ነበር፤ አሁን ግን በዚህ 2 ዓመት ውስጥ ከፍተኛ እንቅስቃሴ ላይ እንዳለ እያየን ነው፡፡ ከእይታ ውጭ የሆኑ ወጣቶች አሉ፡፡ የዚህ መሰረታዊ ችግርም በአካባቢው የተፈጠረው የፀጥታ ችግር ነው፡፡የሚመለከተው አካልም ህገወጦችን አድኖ ለመያዝ ምቹ ሁኔታ የለውም፡፡
ኢሳያስ ገላው
ኂሩት መለሰ
ፀሐይ ጫኔ
























