የኤምፖክስ ተህዋሲ በኢትዮጵያ መገኘቱ ተረጋገጠ
Description
በኢትዮጵያ “ኤምፖክስ” ተብሎ በሚጠራው ተሀዋሲ የተያዘ ሰው ኦሮሚያ ክልል ሞያሌ አከባቢ መገኘቱን የጤና ሚኒስቴር ትናንት አስታውቋል። የአከባቢው የጤና ባለሙያ ለዶይቼ ቬለ እንደገለጹት የበሽታው ምልክት የተወሰኑ ሰዎች ላይ ብታይም በተዋህሲው መያዝ አለመያዛቸው ገና በምርመራ እስኪረጋገጥ ይጠበቃል፡፡ የኢትዮጵያ ጤና ባለሙያዎች ያነሱትን የደመወዝና ጥቅማጥቅም ጥያቄዎችን ተከትኮ የጤና ዘርፉ አከባቢ አለመረጋጋት በሚስተዋልበት ባሁን ወቅት በሽታው መከሰቱ ስጋት አጭሯል፡፡ በኢትዮጵያ ጤና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶ/ር መቅደስ ዳባ ተረጋግጦ በሚኒስቴሩ በኩል ትናንት በተሰራጨው መግለጫ በኤምፖክስ የተያዘ ሰው በኢትዮጵያ ስለመገኘቱ በኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢኒስቲትዩት ተረጋግጧል፡፡ በኦሮሚያ ክልል ሞያሌ ከተማ በ21 ቀን እድሜ ጨቅላ ህጻን ላይ ተዋሲው መገኘቱ ከተረጋገጠ በኋላ በህጻኑ እናትም ላይ ቫይረሱ ስለመገኘቱም የጤና ሚኒስቴር አረጋግጧል፡፡
አስተያየታቸውን ለዶይቼ ቬለ የሰጡ የሞያሌ ሆስፒታል የውስጥ ደዌ ስፔሻሊስ ሀኪም ዶ/ር ሊበን ዲዳ ተዋሲው ምንም እንኳ ስርጭት ባያሳይም ከዚህ በፊትም ታይቶ እንዳይሰራጭ በቁጥጥር ስር ውሎ ነበር፡፡ “ከዚህ በፊት በፈረንጆቹ 2022 የዚህ ተዋሲ ተጠቂ ስድስት ሰዎች ተገኝተው ነበር፡፡ በወቅቱ በተወሰኑ ሰዎች ላይ ምልክቶቹን ብናይም የላቦራቶሪ ችግር ስላለ አላረጋገጥንም ነበር፡፡ አከባቢው ድንበር ላይ ስለሆነ ሰው ከዚህ ኬንያ ከኬንያም ወደዚህ ስለሚመጣ ወዲያ ወዲህ እያሉ ይታከማሉ፡፡ ከዚያን በመሃል ጠፍቶ ቆይቶ ነው አሁን ሰሞኑን አንዳንድ ሰዎች ላይ መታየት የጀመረው፡፡ የ25 ቀን ጨቅላ ህጻን ላይም ምልክት መታየቱን ተከትሎ ነው ናሙናውን ወደ አዲስ አበባ ልከን በተዋሲው መጠቃቱ የተረጋገጠው” ብለዋል፡፡
በአከባቢው ስላለው የተዋሲው ስርጭት ስጋትን በተመለከተም አስተያየታቸውን ያከሉት ሀኪሙ በሽታው እንዳይሰራጭ ለመግታት ርብርብ እንደሚጠይቅ ነው ያመለከቱት፡፡ “ተዋሲው በጨቅላ ህጻኑ ላይ ብረጋገጥም ተመሳሳይ ምልክት ያሳዩ ግለሰቦች አሉ” በማለት አስተያየታቸውን የሰጡት ባለሙያው፤ የጨቅላ ህጻኑ እናት አባትን ጨምሮ አራት ሰዎች ላይ ምልክቶቹ ጎልተው መታየቱን ጠቁመዋል፡፡ በትኩሳና እራስ ምታት ምልክት የሚጀምረው ኤምፖክስ በሶስት ቀናት ውስጥ ሰውነት ላይ የሚወጡ መግል የያዙ ሽፍታዎች እና የጡንጫ መደካከምን እንደሚያስከትሉም አስረድተው፤ ምልክቱ የታየባቸውን ሰውች ወደ መለየት እንዲገባ እና የድጋፍ ርብርብ እንዲደረግ ጠይቀዋል፡፡የዝንጀሮ ፈንጣጣ (Mpox) ምንነት እና ኢትዮጵያ በሽታውን ለመከለከል የጀመረችው ጥረት
የጤና ሚኒስቴር በትናንትናው መግለጫው በሽታው ወደ አገር ውስጥ እንዳይገባ በህብረተሰብ ጤና ኢኒስቲትዩት በኩል ቅድመ ዝግጅት ስደረግ መቆየቱንና በበሽታው የተያዙና ምልክቱን ያሳዩ ወይም ንክኪ ያላቸውን ከህብረተሰቡ ለመለየት ማቆያዎች በተለያዩ ተቋማት መዘጋጀታቸውንም ጠቁሟል፡፡ ሽፍታ፣ ሳል፣ ትኩሳት፣ የራስ ምታት፣ ድካምና የጀርባ ህመምን የመሳሰሉ ምልክቶችን በማሳየት በተለያዩ የአፍሪካ አገራት ተሰራጭቶ የቆየው ኤምፖክስ ዋና መስሪያ ቤቱን አዲስ አበባ ላይ ባደረገው የአፍሪካ በሽታ መከላከልና መቆጣጠር ማዕከል እና በዓለም ጤና ድርጅት ትብብር በሽታውን ለመቆጣጠር ስራዎች እየተሰሩም ነው ተብሏል፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥ የበሽታው መከሰት የተሰማው የኢትዮጵያ የጤና ባለሙያዎች አሉብን ባሉት የደመወዝና ጥቅማትቅም ጥያቄ በበርካታ የጤና ተቋማት አለመረጋጋት በሚታይበት ባሁን ወቅት ሲሆን ይህ ደግሞ ለሀኪሞችም ሆነ በሽታዎችን ለሚቆጣጠሩ የጤና ተቋማት ፈታኝ እንዳይሆን ስጋት አለ፡፡ ስሜ ይቆይ ብለው አስተያየታቸውን ለዶይቼ ቬለ የሰጡ አንድ የጤና ባለሙያ እንዳሉትም፤ “ቶሎ መቆጣጠር ክልተቻለ ከሁላችንም አንጻር ይሄ ከባድ ነው፡፡ ለሁሉም የተሻለ መንገድ ቶሎ ስምምነት ላይ በመድረስ ሀኪሞች የሚያነሱትን ጥያቄ ማዕከል በማድረግ ሁሉም ወደ ስራ እንዲመለስ ማድረግ ነው” ሲሉም አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡
ሥዩም ጌቱ
አዜብ ታደሰ
ታምራት ዲንሳ
























