በሰሜን ሸዋ ዞን፤ ወራጃርሶ ወረዳ ታጣቂዎች ያደረሱት ጥቃት
Description
በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ወራጃርሶ ወረዳ ጊርሚጎባ ቀበሌ መስከረም 29 ቀን 2018 ዓ.ም ታጣቂዎች ባደረሱት ድንገተኛ ጥቃት የንጹሃን ህይወት ማለፉ ተነግሯል፡፡ በአከባቢው ታጣቂዎች አዘናግተው አደረሱ በተባለው በዚህ ጥቃት በርካታ የገበሬማህበሩ ቤቶች መቃጠላቸውና ታግተው የተወሰዱ ሰዎች እንዲሁም የተዘረፉ ንብረቶችም መኖራቸውን ተጎጂዎች እና የአከባቢው ባለስልጣናት ለዶይቼ ቬለ አረጋግጠዋል፡፡
መስከረም 29 ቀን 2018 ዓ.ም. ንጋቱን ሰሜን ሸዋ ዞን ወራጃርሶ ወረዳ ጊርሚጎባ ቀበሌ ዘባ በሚባል ልዩ ስፍራ ታጣቂዎች ባደረሱት ጥቃት ከፍተኛ ጉዳት መድረሱን የአከባቢው ነዋሪ የአይን እማኞች ተናግረዋል፡፡ ከትናንት ሓሙስ ማለዳው ጥቃት መትረፋቸውን ገልጸው አስተያየታቸውን የሰጡን የአይን እማኝ የአከባቢው ነዋሪ ከንጋቱ 11 ሰዓት ላይ ከየት መጣ የማይባልና በማያውቁት የታጠቀ ቡድን በደረሰው ድንገተኛ ጥቃት የሰዎች ህይወት አልፈዋል፤ ንብረትም በከፊል ስወድም ሌላውም በጥቃት አድራሾቹ ታጣቂዎች ተወስዷል፡፡ ለደህንነታቸው ስባል ስማቸውን ከመጥቀስ የተቆጠቡት አስተያየት ሰጪ የአይን እማኝ የአከባቢው ነዋሪ፤ “በተኛንበት ስለያዙን የጥቃት አድራሾቹን ታጣቂዎች ማንነት አናቀውቅም” በማለት በትናንት ማለዳው ጥቃት አራት ሰዎች ሞተው አራት ሰዎች ታግተው ስወሰዱ በግምት ከ150 በላይ ቤቶች በታጣቂዎቹ በቃጠሎ እንዲወድሙ ተደርጓልም ነው ያሉት፡፡
በታጣቂዎቹ ድንገተኛ ጥቃት የተመሰቃቀለው ሕይወት
የሞቱት ንጹሃን ዜጎች ትናንት በአከባቢው በሚገኘው ሐሮ መድሃንያለም መቀበራቸውን የገለጹት የአይን እማኙ ታግተው የተወሰዱት ግን ምን ውስጥ እንዳሉ እስካሁን አለመታወቁን ዛሬ በሰጡን አስተያየት ገልጸዋል፡፡ “አንዲት እናትና አባቷን ይዘዋት ሄደዋል፤ ሌሎቹን ደግሞ ከብቶቻቸውን ስነዱባቸው ባለቤቶቹንም አብረው ነው ይዘዋቸው የሄዱት” በማለት እነሱ አሁን ምን አይነት ሁኔታ ውስጥ እንደሆኑ እንደማይታወቅ ገልጸዋል፡፡ አከባቢው ላይ የተፈጠረውን አለመረጋጋት ተከትሎም በርካታ የቀበሌዋ ነዋሪዎች መኖሪያ አከባቢያቸውን ለቀው ወደ ወረዳዋ ዋና ከተማ ጎሃጽዮን መሸሻቸውን አስረድተዋል፡፡
የጥቃቱ መደጋገም ያሳደረው ስጋት
ከአከባቢው ቤተሰቦቻቸውን እያሸሹ መሆኑን ገልጸው አስተያየታቸውን የሰጡን ሌላው የአከባቢው ነዋሪ በፊናቸው መሰል ጥቃቶቹ በተደጋጋሚ የሚከሰቱ እየሆኑ የሚያደርሰውም ጉዳት እየከፋ ነው ይላሉ፡፡ “በተለያዬ ጊዜ የዛሬ ሦስት ወርም እንዲሁ ሰው ስገድሉ ነበር በዚያም ዘጠን ሰው ሞተዋል” በማለት ትናንት የተፈጠረው ጥቃትም ሰዎች በተኙበት ወደ 200 ቤቶች ተቃጥለው በርካታ የገበሬ ማህበሩ ከብቶች በታጣቂዎቹ መነዳታቸውን ገልጸዋል፡፡ ታግተው የተወሰዱ ሰዎች ቁጥርም አይታወቅም የሚሉት እኚህ አስተያየት ሰጪ የስም ዝርዝራቸውን በመጥቀስ አራት ሰዎች በዚሁ በትናንቱ ጥቃት መገደላቸውን
አመልክተዋል፡፡ “ጥቃቱን ያደረሰው ሸነ ነው” ሲሉ የገለጹት አስተያየት ሰጪው መሄጃ የሌለው ያሉት ህዝቡ ከዚህ በፊትም ግንቦት ወር ላይ በተመሳሳይ ሁኔታ ታጣቂዎች በደፈጣ ባደረሱት ጥቃት የዘጠን ሰዎች ህይወት ማለፉን አስታውሰዋል፡፡
ሌላም አስተያየት ሰጪ የአከባቢው ነዋሪ ፤ “ትናንት ማለዳ በተኛንበት ተኩስ ጀመሩ ኦነግ ሸኔ የሚባሉ ታጣቂዎች ናቸው፡፡ በዚያን ሰዓት ሰው ተደናገጠና አራት ሰው ተጎዳብን” ሲሉ መሰል ጥቃት አምናም በተመሳሳይ ሁኔታ አጋምሳ በምትባል የአከባቢው ጎጥ ላይ በተፈፀመ ጥቃት ሰባት ሰዎች መገደላቸውን ጠቁመዋል፡፡ በትናንት ጥቃቱ የመንግስት የፀጥታ አካላት በሰዓቱ አከባቢው ላይ አለመድረሳቸውን የገለጹት ተጎጂ አስተያየት ሰጪው የአከባቢው ነዋሪ በርካታ ሰው አሁን ላይ ከአከባቢው እየተሰደደ ቢሆንም መግቢያ ግን የሌለው ማህበረሰብ ነው ሲሉ የመፍትሄ ያለ ብለዋል፡፡
የአከባቢው የባለስልጣን ምላሽ
ዶይቼ ቬለ ስለጥቃቱ የጠየቃቸው የቀበሌው አስተዳዳሪ መብራቱ ንጉሴ የድርጊቱን መፈጸም አረጋግጠው በሰዓቱ የመንግስት የፀጥታ ኃይሎች አከባቢው ላይ አለመስፈራቸው በስፍራው ላይ ለነበሩ ጥቂት ሚሊሻዎች ነገሮችን ከባድ ማድረጉ ማህበረሰቡን ለጥቃቱ ዳርጎታል ብለዋል፡፡ “የድርጊቱ መፈጸም ተጨባችና እውነት ነው” ያሉት የአከባቢው ባለስልጠን አከባቢው አባይ በረሃ ውስጥ በአማራ እና ኦሮሚያ ክልሎች አዋሳኝ አከባቢ ሆኖ በኦሮሚያ ክልል ውስጥ የሚገኝ ስፍራ ነው ብለዋል፡፡ ጥቃቱን “የጠላት ኃይል” ያሉት የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት ታጣቂዎች ማድረሳቸውን የጠቆሙት አቶ መብራቱ በትናንት ማለዳው ጥቃት አራት ሰዎች መገደላቸውንና ስድስት ሰዎች ታግተው መወሰዳቸውን ብሎም 50 ቤቶች በቃጠሎ መውደማቸውን እና 81 የቤት እንስሳት በታጣቂዎቹ መወሰዳቸውን እስካሁን እንደተለየ አረጋግጠዋል፡፡ በጥቃቱ ወቅት የፀጥታ ኃይል ወደስፍራው እንዲላክ ለወረዳ ጥያቄ ብቀርብም የወረዳ ከተማም ተመሳሳይ ስጋት ያለበት በመሆኑ መከላከያ ከአጎራባች ወረዳ ኩዩ ወረዳ ልደርስ ሲል በመንገድ ላይ አዋሬ ጎርጄ በሚባል ቀበሌ ተኩስ ተከፍቶባቸው መከላከያም በሰዓቱ ልደርስልን አልቻለም ብለዋል፡፡
ዶይቼ ቬለ ሰላማዊ ነዋሪዎቹ ላይ ጥቃት የፈፀመው የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ነጻነት ሰራዊት ታጣቂዎች ናቸው ማለታቸውን ተከትሎ ከታጣቂ ቡድኑ ወገን ማረጋገጫም ይሁን ማስተባበያ ለማግኘት ያደረገው ጥረት ለዛሬ አልሰመረም፡፡ የአከባቢው ባለስልጣኑ እንዳሉት ግን በቀጣይ የማህበረሰቡ ደህንነት በዘላቂነት ለመጠበቅ ውይይት እየተደረገ ነው፡፡ ዶይቼ ቬለ ሰላማዊ ነዋሪዎቹ ላይ ጥቃት የፈፀመው የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት ታጣቂዎች ናቸው ማለታቸውን ተከትሎ የኦነሰ ከፍተኛ አዛዥ አማካሪ ከሆኑት አቶ ጅሬኛ ጉዴታ ጥያቄውን ያቀረበ ሲሆን ታጣቂዎቻቸው በንጹሃን ዜጎች ላይ መሰል ጥቃት አልፈጸሙም በማለት አስተባብለዋል፡፡
ሥዩም ጌቱ
አዜብ ታደሰ
ፀሐይ ጫኔ